የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አቶ ሙስጠፌ መሐመድና ባልደረቦቻቸውን ሸለመች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አቶ ሙስጠፌ መሐመድና ባልደረቦቻቸውን ሸለመች
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 28/2011 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሱማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድና ሌሎች ባልደረቦች ሽልማት አበረከተች። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሱማሌ ክልል ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መቃሪዎስ ሽልማቱን ለአዲሱ የሱማሌ ርዕሰ መስተዳድርና ባልደረቦቻቸው ያበረከቱት በተለይም አዲሱ አስተዳደር ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት በተነሳው ረብሻ በጅግጅጋና አካባቢው በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና የሃይማኖት አባቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል። የቀድሞው አስተዳደር ከተለወጠ በኋላም በአቶ ሙሰጠፌ መሐመድ የሚመራው አስተዳድር የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲጠገኑ የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ማድረጋቸውም ተወስቷል። በወቅቱ ጉዳት ከደረሰባቸው አብያተ ክርሰቲያናት መካከል ለአብነትም የጅግጅጋ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን በአዲስ መልክ ተሰርታ ተመርቃለች። አቶ ሙስጠፌ መሐመድ አብያተ ክርስቲያናቱ እንዲጠገኑ የፋይናንስና የሞራል ድጋፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪ በክልሉ የጸጥታ አካላት ለአብያተ ክርስቲያናቱ ጥበቃ እንዲያደርጉላቸውም እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህም ዛሬ በጅግጀጋ በተካሄደው የኦሮሞና የሱማሌ የህዝብ ለህዝብ መድረክ ላይ የተገኙት የቤተክርስቲያኗ አባቶች ርዕሰ መስተዳድሩን ለማመሰገን የቤተክርስቲያኗን የክብር ካባ ሸልሟቸዋል። በስፍራው የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም ለሰላም ባላቸው ቁርጠኝነት ተመሳሳይ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።