ቀጥታ፡

የሁላችንም የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ቀን ከሌት እንሰራለን- የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 28/2011የሁላችንም የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ቀን ከሌት እንሰራለን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ወንድማማችነትን በማጠናከር የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ለኢትዮጵያ ዋልታና ማገር ለመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የኦሮሞና ሶማሌ ህዝብ የህዝብ ለህዝብ ምክክር መድረክ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን የፌዴራል ተወካዮች፣ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ከሁለቱ ክልል የተውጣጡ የማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል። በዚሁ ወቅት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት፤ ኦሮሞና ሶማሌ በድርሰትና የፈጠራ ታሪክ አንድ የሚሆኑ ሳይሆኑ በተፈጥሮ በአንድ ትልም የተፈጠሩ በአንድነት የኖሩና የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። ባለፈው 100 አመት በርካታ ፈተናዎችን በአንድነት በመጋፈጥ አንዱ ለአንዱ መከታ በመሆን ለእኩልነትና ለነፃነት መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰው፤ ''የዘመኑ ትውልድ ጭቆናን በጋራ ታግሎ ጥሏል'' ብለዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ ''የተገኘውን ነፃነትና እኩልነት ወደተሻለ ደረጃ የማሸጋገር ኃላፊነት አለብን'' በማለት፤ ''ግለሰቦች እንጂ ህዝብ እንደህዝብ አልተጋጨም አልፎ አልፎ በወሰን አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮች እንኳን ቢኖሩ በቱባ ባህላችን እየፈታን አንድነታችንን ማጠናከር ይገባልም '' ሲሉ ገልጸዋል። ''አሁን ያለው የፌዴራሊዝም ስርዓት እውነተኛ እንዲሆን ሁሉንም የምትመስል ኢትዮጵያ መፍጠር አለብን'' ብለዋል። ኢትዮጵያዊ ማንነት የአንድ ሰፈር ማንነት እንዳልሆነ ገልፀው፤ የሁሉም ድምፅ በፌዴራልና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መወከል እንዳለበት ተናግረዋል። ''የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠናከር ወንድማማችነት እንዲጎለብት ድህነት እንዲቀረፍ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ወደፊት መራመድ አለብን'' ሲሉ አስገንዝበዋል። የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እያከናወኑ ያለውን ስራ አድንቀው በጋራ በመሆን የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ቀን ከሌት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ''ከፊታችን ትልቅ ተስፋ አለን'' ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ''ከጉዟችን ሊያስቆሙን የሚቃዡ ኃይሎች አይሳካላቸውም፤ ለኢትዮጵያውያን የሚያዋጣው መደማመጥና ሆደ-ሰፊነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሀሳብን ማራመድ ብቸኛው አማራጭ ነው'' ብለዋል። አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው ''እንግዶቹን ወደክልላችሁ እንጂ ወደሌላ ክልል አይደለም የመጣችሁት'' ብለዋቸዋል። ''ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካ አሻጥር ግጭቶች ተፈጥረው ብዙ ህዝብ መጎዳቱን አስታውሰው ዛሬ ከችግሩ ወጥተን በጋራ መሆናችን የሚያስደስት ነው'' ሲሉም ተናግረዋል። ሶማሌና ኦሮሞ ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚዋሰን በመሆኑ በውሃና በግጦሽ የሚፈጠሩ ችግሮች በሽማግሌና በአመራሮች ውይይት መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል። የሁለቱ ህዝቦች ወንድማማችነት ለዘመናት የቆየ መሆኑን ገልፀው፤ ''አሁንም ወንድማማችነቱን በማጠናከር ለአንዲት አገር ዋልታ መሆን አለብን ይህም ለመላው አፍሪካ የሚተርፍ እድገትና ብልፅግና ያመጣል ነው'' ያሉት። በሁለቱም   ወገን  በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ከጊዜያዊ ስሜት እንዲወጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ተፈናቃዮች ንብረቶቻቸውን እንዲያገኙ እየሰራን ነው ወደፊትም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ቃል ገብተዋል። የኦሮሞና ሶማሌ የህዝብ ለህዝብ መድረክ በዚህ አመት ሚያዚያ ወር ላይ በአዳማ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል። በመድረኩም ከሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋዞች እና የኦብነግ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፎ አድርገው የነበረ ሲሆን  በሁለቱ ክልሎችና በአገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም