መገናኛ ብዙሃን የአገሪቷን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ለማሻሻል ሚዛናዊ ሆነው መዘገብ ይኖርባቸዋል-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የአገሪቷን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ለማሻሻል ሚዛናዊ ሆነው መዘገብ ይኖርባቸዋል-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ትብብሯን ለማሻሻል በምታደርገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊና ችግሮችን ማሳየት የሚያስችል ብቃት ሊኖራቸው እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው “የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና የሚዲያ ሚና “ በሚል ርዕስ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ያዘጋጀው የሁለት ቀናት ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል። ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ "መገናኛ ብዙሃን ለአንድ አገር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እድገትና መሻሻል ወሳኝ ናቸው"። በቂ መረጃ ያለው ኅብረተሰብ ለመፍጠር የመገናኛ ብሃን አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ "በዲፕሎማሲው ዓለምም ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዳለባቸው" ገልጸዋል። አገሪቷ ዲፕሎማሲዋን በማጎልበትና ጥቅሟን በማስጠበቅ ረገድ መገናኛ ብዙኃን የማይተካ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ "የሚታዩ ችግሮችንና መልካም ስራዎችን ሚዛናዊ ሆኖ ማቅረብ ይገባል" ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የኅብረተሰቡን የመረጃ ተደራሽነት ለማሳደግና ፍላጎት ለማርካት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በቅንጅት አንደሚሰራ ጠቁመዋል። መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች በእውቀት ላይ ተመስርተው ነባራዊ ሁኔታዎችን በመተንተን ለአገሪቷ ልማት፣ ሰላምና ደህንነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ምሁር ዶክተር ቶን ቪን በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን መንግስትን ከመንግስት፣ መንግስትን ከኅብረተሰብ እንዲሁም ኅብረተሰብን ከኅብረተሰብ "የሚያገናኝ ድልድይ መሆን አለበት" ብለዋል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤትም የሚኒስቴሩ አይንና ጆሮ መሆን ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ በቂ መረጃ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበትም ጠቁመዋል ምሁሩ። መገናኛ ብዙሃን ግልጽነት በተሞላበት መንገድ መረጃዎችን በማሰራጨት ለመንግስትና ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ መረጃዎችን የሚጠቁም፤ ለአገር ፖሊሲ ቀረጻ ትልቅ ሚና የሚጫወት ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።