ኮሌጁ ያሰለጠናቸው መኮንኖች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሌጁ ያሰለጠናቸው መኮንኖች አስመረቀ
ሀዋሳ ሐምሌ 27/2011 የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ለሁለተኛ ጊዜ በዲፕሎማ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን መኮንኖች ዛሬ አስመረቀ። በምረቃ ስነስርዓት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኤልያስ ሽኩር እንዳሉት ሰላማዊ የነበረው የደቡብ ክልል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጸጥታ ችግር ገጥሞት ቆይቷል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የጸጥታ ችግር በፍቅር ተከባብረውና ተረዳድተው በሚኖሩ ህዝቦች ዘንድ ስጋት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። የህዝቡን አንድነት ፣ብዝሀነትና አብሮነትና በሀገር ደረጃ ክልሉ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የማይዋጥላቸው አካላት በፈጠሩት ችግር ጉዳት ማስከተሉን አመልክተዋል። የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከፌዴራል ፖሊስና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል የዛሬ ምሩቃን በቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት በመጠቀም ህዝቡን ከስጋት ለማላቀቅ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወልደሚካኤል በበኩላቸው በክልሉ የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ የመላው ህዝብና የተለያዩ መንግስታዊ አካላት አስተዋጽኦ የሚያስፈልግ ቢሆንም በዋናነት የፖሊስ ሰራዊት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። ይህን የህዝብን ሰላም የማስከበር ስራ በኃላፊነት የተቀበለው የፖሊስ ሰራዊት ከብሄር ፣ ኃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ችግሮች ራሱን ማራቅ እንደሚገባ አመልክተዋል። የዛሬ ተመራቂዎችም የተጣለባችውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ራሳቸውን በመልካም ስነምግባር በማነጽ ወንጀልን ለመከላከል በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ሰልጣኞቹ በኮሌጁ ቆይታቸው ወቅት ንድፈ ሀሳብን በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንደተሰጣቸው የገለጹት ደግሞ የኮሌጁ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጃዋር ሙሳ ናቸው። ከክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ሌሎች አካባቢዎች ተወጣጥተው በኮሌጁ በረዳት ኢንስፔክተርነት ማዕረግ በዲፕሎማ መርሀ ግብር ዛሬ የተመረቁት 147 ሰልጣኞች መሆናቸውን ተናግረዋል። ከተመራቂዎቹ መካከልም 18 ሴቶች ይገኙበታል። በማዕረግ ከተመረቁ መኮንኖች ውስጥ ረዳት ኢንስፔክተር ምንትዋብ አሸናፊ በሰጠችው አስተያየት በቆይታዋ የቀሰመችውን እውቀት ስራ ላይ በማዋል ህዝቡን ለማገልገል የድርሻዋን እንደምትወጣ ተናግራለች። ሌላው ተመራቂ ረዳት ኢንስፔክተር ስራቸው ብርሀኑ በበኩሉ “ከወገንተኝነት ነጻ በመሆን በቅንነት ህዝባችንን በማገልገል ወንጀልን ለመከላከል እሰራለሁ “ብሏል።