ቀጥታ፡

በቀጣዩ ጨዋታ ሩዋንዳን እንገጥማለን --- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ

ድሬዳዋ ሐምሌ 27/2011 በቻን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ጅቡቲን አሸንፈው በቀጣዩ ጨዋታ ሩዋንዳን እንደሚገጥሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስታራክተር አብረሃም መብራቱ ተናገረ። በቻን የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሣምንት በፊት ከጅቡቲ ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድ ለባዶ አሸንፎ የመልስ ጨዋታውን ደግሞ ነገ ድሬዳዋ ላይ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን ያደረገው የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ኢንስታራክተር አብረሃም መብራቱ ለኢዜአ እንደገለጸው አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ በማድረጋቸው የነገውን ጨዋታ ለማሸናፍ ተሰናድተዋል። “የጅቡቲ አቻ ቡድን ለዓመታት በታዳጊ ወጣቶች ላይ በሰራው ስራ ጠንካራ ቡድን መደራጀቱን መካድ አይቻልም፤ በጅቡቲ ላይ በነበረን ጨዋታ ፈትኖናል “ብሏል፡፡ በወቅቱ የነበረው ከፍተኛ ሙቀት ተጫዋቾችን እንዳስጨነቃቸው ኢንስትራክተር አብረሃም መብራቱ አስታውሷል። ነገር ግን ለመልሱ ጨዋታ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በድሬዳዋ በቀን ሁለት ጊዜ ያደረጉት ልምምድ ተጫዋቾችን በአካልና በስነ ልቡና ዝግጁ ያደረገ በመሆኑ ጨዋታውን አሸንፈው ከሩዋንዳ ጋር እንደሚገጥሙ ነው የገለጸው፡፡ እንደኢንስትራክተር አብረሃም ገለፃ የድሬዳዋ አስተዳደር ፣ የስፖርት ኮሚሽንና አመራሮች እንዲሁም የድሬዳዋ ህዝብ ለብሔራዊ ቡድኑ ያደረገው አቀባበልና መስተንግዶ ለነገው ጨዋታ ማሸነፍ ትልቅ ስንቅ ሆኗቸዋል፡፡ በአጥቂ ስፍራ የሚጫወተው የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋች አማኑኤል ገብረሚኪኤል አልጣኛቸው የሚላቸውን በሙሉ ሜዳ ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ አማኑኤል እንዳለው ነገ ጨዋታውን አሸንፈው የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስደሰት ተዘጋጅተዋል። “ባለፈው ሣምንት የጅቡቲ ሜዳ አርቴፊሻል መሆኑና ሙቀቱ ከፍተኛ ስለነበር ለመጫወት አስቸግሮን ነበር፤ እዛ ያጋጠመን ነገ በሜዳችን ስለማይኖር እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነኝ” ብሏል፡፡ መላው የስፖርት ቤተሰብ እያደረጉላቸው ላለው መስተንግዶ አመስግኗል፡፡ የድሬዳዋ ወጣቶች ለጅቡቲ ብሔራዊ ቡድንም አቀባበል አድረገውለታል፤ ለቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ባህላዊ ልብስ አበርክተዋል ፤ባህላዊ የኪነት ቡድኖችም ለቡድኑ የደመቀ ዝግጅት አቅርበዋል፡፡   የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አብዲ መሐመድ ለኢዜአ ሪፖርተር በሰጠው በሰጠው አስተያየት የድሬዳዋን አየርና ሜዳ ለመለማመድ ከሣምንት በፊት በመምጣት ጥሩ ልምምድና ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግሯል።   “በጨዋታ ማሸነፍም መሸነፍም ያለ ነገር ነው፤ እዚህ የመጣው ግን ለማሸነፍ ነው፤ ለዚህም ተዘጋጅተናል” ብሏል፡፡   “የህዝቡ አቀባበል፣ ፍቅርና መስተንግዶ በትክክል ወደ ሁለተኛ ሀገሬ እንደመጣሁ አረጋግጦልኛል “ ያለው ደግሞ ሌላው የጅቡቲ ተጫዋች ሰኢድ ሙሣ ነው፡፡   በቀን ሶስቴ ልምምድ ማድረጋቸውንና ዛሬ የመጨረሻቸው መሆኑን ጠቅሶ ነገ አሸንፈው ህዝባቸውን እንደሚያስደስቱ ገልጿል።   ለሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የባህላዊ አልባሳት የሸለሙት ወጣቶች አስተባባሪ ኢብራሂም ሰመሬ እንዳለው ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ይበልጥ ለማፅናት፣ የሁለቱን ወንድማማች ሀገራት ግንኙነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለመጎልበት በማሰብ የበኩላቸውን አድረገዋል።   “ ብሔራዊ ቡድናችን ከዓመታት በኋላ ድሬዳዋ ላይ የሚያደርገው ጨዋታ ቀጣይነት እንዲኖረው በነገው ጨዋታ ፍፁም በፍቅርና በማይረሳ ትዝታ ታጅቦ እንዲኪያሄድ ኃላፊነታችንን እንወጣለን” ብሏል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም