የቡና የወጪ ንግድ ገቢ ቀንሷል

170
ሀምሌ 27/2011 ከቡና የወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ ባለፉት አስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መውረዱ ተገለጸ። ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከቡናና ሻይ እንዲሁም ቅመማ ቅመም ምርቶች የውጭ ገበያ ያገኘችው ገቢ ቅናሽ አሳይቷል። ይህን አስመልክቶ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ውይይት በቢሺፍቱ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የ2011 በጀት ዓመት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በተለይም ወደ ውጭ የሚላከው የቡና ምርት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተገልጿል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አዱኛ ደበላ እንደተናገሩት ውጤቱ ላለፉት 13 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል። በዘርፉ ላጋጠመው የገበያ መቀነስ ቅሸባ (የተደራጀ የቡና ዝርፊያ)፣ የቡና ገዢ አገራት ውል የመሰረዝና ወደ ውጪ እሴት ጨምሮ አለመላክ ምክንያት ናቸው ብለዋል። ችግሩን ለማስተካከልም የቡናና ሻይ ባለስልጣን የኢትዮጵያን ቡና እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅና የቡና አምራች አርሶ አደሮችንም ተጠቃሚ ለማድረግ ከአጋሮች ጋር በቅንጅት እንድሚሰራ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በ2010 በጀት ዓመት 238 ሺህ 465 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 838 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ስታገኝ፤ በተጠናቀቀው የ2011 በጀት ዓመት ደግሞ 230 ሺህ 764 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 763 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች። ምርቱ ከተላከባቸው አገራት መካከል አሜሪካ፣ ሳዑዲአረቢያ እና ጀርመን ቀዳሚውን ደረጃ ይዘዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም