ቀጥታ፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ የአሰራር ማሻሻያዎች ባለሃብቶችን የሚያበረታቱ ናቸው ተባለ

አዲስ  አበባ  ሐምሌ  27/2011 የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማሻሻያ እየተደረገባቸው ያሉ የኢንቨስትመንት ህጎችና አሰራሮች በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገለጸ። የሀገር ውስጥ ባለሃብቱን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ የመጀመሪያው "የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፎረም" በአዲስ አበባ ተካሂዷል። መንግስት የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨሰትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገ ይገኛል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን እንዳሉት፤ ከ40 በላይ አሰራሮች እና የህግ ማቀፎች ከጊዜና ወጭ አንፃር ማሻሻያ እየተደረገባቸው ነው። ማሻሻያው የግል ባለሃብቱን ፈቃድ አሰጣጥ በማቀላጠፍ በስፋት ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ የሚያበረታቱ መሆናቸው ታውቋል። እነዚህ የህግና አሰራር ማሻሻያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ በተለይ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች የሚያበረታቱ መሆናቸውን አቶ ተመስገን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለማሳደግ የመንግስት ስራ ብቻውን በቂ አለመሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ታደሰ በበኩላቸው፤ የሚዘጋጁ የኢንቨስትመንት ህጎች የማምረቻ ዘርፉን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው ብለዋል። በአግሮ ፕሮሰሲንና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ከ6 እስከ 15 ዓመት የግብር እፎይታ ጊዜ እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል። በስራ እድል ፈጠራ፣ በተዬክኖሎጂ ሽግግርና የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኙ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የማምረቻ መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ይፈቀድላቸዋልም ብለዋል። በአነስተኛ ውጭና ቴክኖሎጂ የሚሰሩ የጨርቃጨርቅና አልባሳት የማቅለም ስራ፣ ከደረጃ አንድ በታች ያሉ የኮንስትራክሽን ስራዎችና የአስጎብኝ ድርጅቶች ባሉ ዘርፎች የሀገር ውስጥ ባለሃብቱ ቅድሚያ እንደሚያገኙም ተጠቁሟል። በአንድ አገር ውስጥ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ አስተማማኝ የህግ ማዕቀፍ፣ እንዲሁም በቂ ፋይናንስ መኖር ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለማበረታታት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚታሰብ መረጃዎች ይጠቁማሉ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም