የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ ተካሄደ

84
ነቀምቴ ሐምሌ 27 /2011 የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ተካሄደ። በዞኑ ሳሲጋ ወረዳ የተካሄደው መድረክ የሁለቱን ክልሎች ሕዝቦች ወደ ሰላምና አንድነት ለማምጣት ታስቦ መዘጋጀቱ ተገልጿል። በወረዳው ባረዳ ቀበሌ የተደረገው መድረክ የበሎ ጀገንፎይ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዲንሳ አመንቴ እንደተናገሩትመድረኩ የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል። ለበርካታ ዓመታት አብረው የኖሩ፣የተጋቡና ተመሳሳይ ባህልና ወግ የነበራቸውን ሕዝቦች በማለያየት የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል። የሳሲጋ ወረዳ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ለሚ ጀባ መድረኩ የሕዝቦቹን አንድነት በማጠናከር  ለጋራ ልማትና ዕድገት ለመሥራት የሚነሳሰቡት እንደሆነ ተናግረዋል። የወጣቶች፣ሴቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ንጹህ ልብና ንጹህ አዕምሮ በመያዝ የሰላምና የልማት እንቅስቃሴያቸው የሚያጠናክሩበት መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል። የምስራቅ ወለጋ ዞን ሴቶች፣ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት በየነ በበኩላቸው ሴቶችና ሕፃናት በሰላም እጦት እንዳይጎዱ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ሰላም የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ስለሚጠይቅ ሰላምን ለማረጋገጥ ድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል። የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ደሳለኝ እንደተናገሩት መድረኩ ወደ ቄያቸው የተመለሱ የክልሎቹ  ተወላጆች የመደመር መርህን በመከተል በፍቅርና መቻቻል ላይ የተመሰረተ ሕይወት እንዲመሩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። ሕዝቦቹ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለሰላምና ለልማት መረጋገጥ እንዲሰሩ አስገንዝበዋል። ከሶጌ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ደጊቱ ደንበሻ በሰጡት አስተያየት በአጎራባች ክልሎች ወሰን የተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀል ኑሮአቸውን መናጋቱን ገልጸዋል። መድረኩ አንድነታቸውን በማጠናከር ለሰላምና ልማት የሚያነሳሳ የማነቃቂያ መድረክ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል። በሳሲጋ ወረዳ የላሊሳ በረዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ባይሳ ተገኝ በበኩላቸው መድረኩ ሕዝቦቹን ያቀራረበ ነው ብለዋል። ''አንድነታችን አጠናክረን ቡና መጠራራት፣አንድ ገበያ እንድንጠቀምና አንዱ ለአንዱ እንዲያስብ ያደርጋል'' ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በመድረኩ ከክልሎቹ የተውጣጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ አባ ገዳዎች፣የአገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች፣ሴቶች፣ሃይማኖት አባቶችና አመራሮች ተገኝተዋል። በመድረኩ የክልሎቹ ባህል የሚያንፀባርቁ ሰላምና አንድነትን የሚያንጸባርቁ ድራማ፣ ግጥምና የሙዚቃ ሥራዎች ቀርበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም