ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ 14 ህገወጥ ነጋዴዎች እስከ 11 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ

ሐምሌ 27/20111 በጎንደር ከተማ መንግስት በድጎማ የሚያቀርባቸውን የፍጆታ ሸቀጦች በህገ-ወጥ መንገድ ሲያዘዋወሩ የተገኙ 14 ነጋዴዎች እስከ 11 ዓመት በሚደርስ እስራት መቀጣታቸውን የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ “ህጋዊ የግብይት ስርዓት ለዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ሀሳብ መምሪያው ያዘጋጀው 7ኛው የንግድ ቀን በፓናል ውይይትና በሌሎች ዝግጅቶች ትናንት ተከብሯል፡፡ በዚህ ወቅት የመምሪያው የኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አቶ አብልኝ ሙሉ እንደተናገሩት ነጋዴዎቹ የእስራት ቅጣቱ የተላለፈባቸው የንግድ ህጉን በመተላለፍ በህገ-ወጥ የንግድ ተግባራት ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው። ግለሰቦቹ 200 ሺህ ብር ግምት ያለው የፓልም ዘይትና ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ በድብቅ ሲያጓጉዙ ተገኝተው በተመሰረተባቸው ክስ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኝነተኝነነታቸውን አረጋግጦ ቅጣቱን አስተላልፎባቸዋል። ቅጣቱ የተላለፈው በጥፋታቸው መጠን ከ1 ወር ጀምሮ እስከ 11 ዓመት በሚደርስ እስራት መሆኑን ቡድን መሪው አስታውዋል። የ11ዓመት እስራት ቅጣት የተላለፈው በመኖሪያ ቤቱ በድብቅ ያልተፈቀደለትን መድኃኒት ሲሸጥና ሲያዘዋውር በተገኘ አንድ ግለሰብ ላይ ነው። ይሄው ግለሰብ በተጨማሪ የ5ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎበታል። በሌላም በኩል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መምሪያው ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ፣ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በመደበቅ እጥረት እንዲፈጠር ያደረጉና በሀሰተኛ ሚዛን የተጠቀሙ ከ1ሺ በላይ ነጋዴዎች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህዝብ እንዲማረር ያደረጉ ከ600 በላይ የልኳንዳ ቤቶች፤ የሲሚንቶና የብረት አከፋፋይና ቸርቻሪ ነጋዴዎች መሸጫ መደብሮችን በጊዜያዊነት በማሸግ ዋጋ እንዲያስተካክሉ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም "ያለንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ 776 ህገ ወጥ ነጋዴዎችን በመምከርና በማስተማር ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱ እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል "ብለዋል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ አምሳሉ ደረጀ በበኩላቸው በከተማው የሚስተዋለውን የህገ-ወጥ ንግድ መበራከት የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል። "በኮንትሮባንድ ንግድ ሳቢያ ህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ይደርስ የነበረውን የገበያ ተጽእኖም ተገቢውን ክትትል በማድረግ ችግሩን ለማቃለል እርምጃዎች ተወስደዋል" ብለዋል፡፡ የንግዱ ህብረተሰብ ዘመናዊ የንግድ አሰራሮችን በመከተል በውድድር ላይ የተመሰረተ ጤናማ የንግድ ስርዓት እንዲሰፍን የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው ናቸው፡፡ በከተማው በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ አሊ ሱሌማን እንዳሉት በከተማው ቅዳሜ ገበያ አካባቢ ይካሄድ የነበረውን ህገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግድ መቆጣጠርና ስርዓት ማስያዝ መቻሉ ለህጋዊ ነጋዴው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በከተማው ህገ-ወጥ ንግድን በመቆጣጠር የንግድ ስርዓቱን ፈር ለማስያዝ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ የክፍለ ከተማ የንግድ ማዕከላት እና የስራ ሂደት አስተባባሪዎች በዕለቱ የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡ በጎንደር ከተማ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ 16ሺ 483 ህጋዊ ነጋዴዎች እንደሚገኙና በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሚጠበቅባቸውን 256 ሚሊዮን ብር ግብር መክፈላቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም