የትግራይ ዲያስፖራዎች ዛሬ ችግኝ ተከሉ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ዲያስፖራዎች ዛሬ ችግኝ ተከሉ
መቐለ (ኢዜአ) ሐምሌ 26/2011 - በትግራይ ህዝቡ ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ እየሰጠ ያለውን ትኩረት አዲስ የሚተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ሊያጠናክር እንደሚገባ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ተናገሩ። ዳያስፖራዎቹ ዛሬ ጠዋት መቀሌ በሚገኘው የትግራይ ሰማዕታት ኃውልት ግቢ ውስጥ ችግኝ ተክለዋል። ከአሜሪካ ዳላስ ቴክሳስ የመጡት ዲያስፖራ አቶ ዮሐንስ ተክለብርሃን እንደገለጹት፣ በክልሉ ከሚያስደስቷቸው መልካም ሥራዎች መካከል አንዱ የትግራይ ክልል ህዝብ ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ የሰጠው ትኩረት ነው። “ችግኝ እንደ ህጻን ልጅ በመሆኑ አዲስ በተለይ ለሚተከል ችግኝ ተገቢ እንክብካቤ በማድረግ ለታለመለት ውጤት ማድረስ ያስፈልጋል” ብለዋል። ከስዊድን የመጡት አቶ ኃይለስላሴ አብርሃ በበኩላቸው፣ ከችግኝ ተከላው በተጨማሪ በከተማ ደረጃ ተክሉን የሚከታተልና የሚንከባከብ አካል ሊኖር እንደሚገባ አመልክተዋል። “ መንግስት ለችግኝ ተከላ የሰጠውን ትኩረት ያህል ለእንክብካቤ ሥራ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል” ያሉት ደግሞ ከካናዳ የመጡት ወይዘሮ ጽጌ ገብሩ ናቸው። የካሊፎርኒያ ነዋሪ ዲያስፖራ አቶ ቴዎድሮስ ኪዳነማሪያም በበኩላቸው፣ "የክልሉ ህዝብ ለዘመናት ሲያካሂድ በቆየው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ለደን ሃብት መጨመር የጎላ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል" ብለዋል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፣ በክልሉ ሲካሄድ በቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መደሰታቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በአካል የተመለከቱት ገጽታ ከ14 ዓመት በፊት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ ከነበረው የጎላ ለውጥ እንዳለው ገልጸዋል። ህዝቡ ለዘመናት ያካሄደውን የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለትውልድ የሚተርፍና አሻራውን በተግባር ያሳያበት መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ዳያስፖራዎቹ በአገራቸው ልምላሜ የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አመልክተዋል።