ኤጀንሲው አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት መመሪያ አዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት መመሪያ አዘጋጀ
ሐምሌ 27/2011 የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ አካል ጉዳተኞችን በዘርፉ የሚያሳትፍ መመሪያ ማዘጋጀቱን አስታወቀ። ኤጀንሲው ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችና የልማት ማዕከል ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የአካቶ ትምህርትና ስልጠና መመሪያ ዛሬ ይፋ አድርጓል። በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ደጀን አካል ጉዳተኞችን በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማካተት ለነገ የማይባል አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ኤጀንሲው ከማዕከሉና መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ግብረ ሰናይ ተቋማት ጋር በመሆን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት መመሪያ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል። በዘርፉ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ስርዓት በመዘርጋት የአገሪቱን የቀደመ ስልጣኔ በዘመናዊ መልኩ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ በመጠቆም። እየተዘጋጀ ባለው የትምህርት ፍኖተ ካርታ በተለይ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከፍተኛ ትኩረት ከመሰጠቱ ጋር ተያይዞ አካል ጉዳተኞችን በዘርፉ ማሳተፍ የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም አመልክተዋል። አካል ጉዳተኞች በሁሉም የትምህርትና ስልጠና ተቋም በመሳተፍ እውቀት እንዲያገኙና በአገራቸው እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያደርጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችና የልማት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ መላኩ ተክሌ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በበቂ ሁኔታ እየተሳተፉ አለመሆኑን አንስተዋል። መመሪያው የአካል ጉዳተኞች ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እኩል እንዲሳተፉ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉና ስልጠናውም እነሱን ከግምት ያስገባ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። አካል ጉዳተኞች በስልጠና የሚያገኙትን እውቀት በመጠቀምና አምራች ዜጋ በመሆን ራሳቸውንና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚስችል አሰራር እንደሆነም ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ መመሪያው የአካል ጉዳተኞች በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት ከፌዴራል እስከ ታችኛው መዋቅር ያለውን አሰራር ቀላልና ቀልጣፋ የሚያደርግ ነው።