የፖለቲካ ፓርቲዎች በሶስት አጀንዳዎች ላይ እየተወያዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሶስት አጀንዳዎች ላይ እየተወያዩ ነው
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 26/2011በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አዘጋጅነት ውይይት ማድረግ የጀመሩት የኢትዮጵያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለውይይት ካዘጋጇቸው አጀንዳዎች ውስጥ በሶስቱ ላይ እየተወያዩ ነው። በዛሬው የውይይት መርሃ-ግብር ውይይቱ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ይሁን ወይስ አይሁን በሚል ለረዥም ሰዓታት ክርክር አድርገዋል። ፓርቲ የመሆን ህልውና ሳይረጋገጥ ጊዜ በሚሰጥ አጀንዳ ላይ መወያየት ተገቢ አይደለም የሚሉና ሌሎችም ሃሳቦች ተነስተውም ተከራክረውባቸዋል። የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ፣ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ፣ ለፓርቲዎቹ የሚሰጥ አበልና ጥቅማጥቅም ቅድሚያ ተሰጥቶት ውይይት ሊደረግባቸው እንደሚገባ ነው የውይይቱ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ያነሱት። በሌላ በኩል ለዛሬ የተያዘው የውይይት አጀንዳ ነው መቅረብ ያለበት ወቅታዊ ጉዳዮችን በሌላ ጊዜ ማንሳት ይቻላል የሚለው ሃሳብ ገዥ ሆኖ ፓርቲዎቹ በያዙት አጀንዳ ላይ ውይይታቸውን ቀጥለዋል። በዚህም መሰረት ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሚደረግ ድጋፍ፣ በፓርቲዎች ውህደትና ጥምረት እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ በመወያየት ላይ ናቸው።