ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአዳዲስ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሐምሌ 26 / 2ዐ11 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ተደራሽነትን በማስፋት በአዳዲስ ማእከላት ስራ መጀመሩን አስታወቀ። የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓትን ተደራሽነት ለማስፋት በሀዋሳና በሁመራ የተገነቡት የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማእከላት ተመርቀው ስራ መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ ገልጸዋል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው የተቋሙን የበጀት አመት አፈጻጸም አስመልክተው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የማእከላቱ መገንባት አርሶ አደሮች፣ አቅራቢዎች፣ የህብረት ሥራ ማህበራትና ላኪዎች ወደ አዲስ አበባ መምጣት ሳይገባቸው በነዚህ ማእከላት ተገኝተው ግብይት ማከናወን እንደሚያስችላቸውም አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪ በመቱ ፣ ቡሌ ሆራና ቴፒ እያንዳንዳቸው 152 ሺህ ኩንታል የመያዝ አቅም ያላቸው መጋዘኖች፣ የላቦራቶሪ ፣ የናሙና መውሰጃና ቢሮዎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አውስተዋል፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት 11 ዓመታት በየቅርንጫፎቹ የመጋዘን፣ የላቦራቶሪ ፣ የናሙና መውሰጃና የመሳሰሉት ሥራዎችን የሚያከናውነው ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተረከባቸውና ከግለሰቦች በተከራያቸው መጋዘኖች ነው። በዚህ ዓመት ልዩ ትኩረት ሰጥተን ምርት ገበያው ካለው ተልእኮ አንጻር ደረጃውን የጠበቀ መጋዘንና ተያያዥ ፋሲሊቲዎችን መገንባት ጀምረናል ብለዋል። ባለፉት አመታት የነበሩ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ውስንነቶች እንደነበሩባቸውና ፤ ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዳዲስ አካባቢዎች ግብይት ማስጀመር የሚያስችላቸውን ተግባራት በማከናወን ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በቴፒ አዲስ ቅርንጫፍ መክፈት፣ በነቀምትና በጎንደር የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላትን ስራ ማስጀመር ፣ ግንባታቸው የተጠናቀቀውን የጅማና የአዳማ ግብይት ማዕከላትን ውስጣዊ አደረጃጀት ማሟላት እንዲሁም የመቱና ቡሌ ሆራ የመጋዘን ግንባታዎችን ማጠናቀቅ በእቅድ ተይዞ እንደነበር ዋና ስራ አስፈፃሚው አስታውሰዋል። የግብይት ክንውንን አስመልክቶ በተሰጠው ማብራሪያ፤ ምርት ገበያው በበጀት ዓመቱ 673 ሺህ 057 ቶን ምርት ለማገበያየት እቅድ የነበረው ሲሆን ክንውኑ የአንድ በመቶ ጭማሪ በማሳየት 681 ሺህ 845 ቶን ምርት ተገበያይቷል፡፡ ከተገበያየው ምርት ውስጥ 45 በመቶው ቡና፣ 34 በመቶ ሰሊጥ ነው፡፡ በግብይት ዋጋም 30 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው ምርት ለማገበያየት ታቅዶ ከእቅዱ 11 በመቶ በላይ 33 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር አገበያይቷል፡፡  ይህም ካለፈው ዓመት ክንውን በሦስት በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ የዚህ ዓመት የነጭ ቦሎቄ ግብይት ከእቅዱ በ65 በመቶ አድጎ 600 ሺህ ኩንታል ለማገበያየት አስችሎታል፡፡ በተለይ አኩሪ አተር ግብይቱ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል እንዲፈጸም አስገዳጅ ሆኖ እንዲገባ በመደረጉ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 875 ሺህ ኩንታል ሊገበያይ ችሏል። የሽምብራ ግብይት አስገዳጅ ባይሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ 400 ኩንታል በማገበያየት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ “በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም የምርት ገበያው ቅርንጫፎች 763 ሺህ 151 ቶን ምርት ለመቀበል አቅደን 711 ሺ 850 ቶን ምርት ተቀብለናል፡፡ ይህም የእቅዱን 93 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን ክንውናችን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሦስት በመቶ ብልጫ አለው፡፡” ብለዋል። ምርት ገበያው ከፍተኛ የምርት ቅበላ ባለበት ወቅት የመጋዘን ጥበት ማጋጠም፤ባለፉት የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ በከፍተኛ መጠን ማሽቆልቆል፤ በአየር ንብረት መዛባት የተነሳ የምርት መጠን መቀነስና የጥራት መጓደል በኮንትሮባንድ የተነሳ በጥራጥሬ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ መፈጠሩ በችግር ተነስተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል የመጋዘን ጥበትን ለመቋቋም በጊዚያዊነት መጋዘኖችን መከራየት፤በጥራት አጠባበቅ ላይ የባለድርሻ አካላትን አቅም ማሳደግና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ተጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይ አመት ቀይ ቦሎቄ፣ አረንጓዴ ማሾ አስገዳጅነታቸውን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ግብይታቸውን ማከናወን፤ኑግና ጥጥን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ ማስገባት በእቅድ ተይዘዋል። በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከባንክ ብድር ማግኘት የሚያስችሉ ስራዎችን ተቋሙ እየሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ ወንድማገኘሁ ያብራሩት። በዚህም አርሶ አደሮች ምርታቸውን በምርት ገበያው መጋዘኖች በማከማቸት ከባንኮች ብድር የሚያገኙበት አሰራር በተመረጠ ምርት ወደ ሙከራ ሥራ መግባት የእቅዱ አካል ናቸው፡፡ ምርት ገበያው በሁሉም ቅርንጫፎች ስራውን ሲጀምር የቀጣዩ ዓመት የግብይት መጠን ከዘንድሮው በ23 ከመቶ ብልጫ እንደሚኖረውና 35 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዋጋ የሚኖራቸው 788 ሺህ 910 ቶን ምርት ማገበያየት እንደሚያስችል አቶ ወንድማገኘሁ አስታውቀዋል። በአጠቃላይ ምርት ገበያው ባለፉት 11 ዓመታት 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን ምርት በ237 ቢሊየን ብር ለማገበያየት መቻሉም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም