ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ችግኝ ለመትከል ያሳየችውን ተነሳሽነት በቀጣናው ለማስፋፋት ከአገራቱ ጋር እንደሚሰራ ተመድ ገለጸ

ሐምሌ 26/2011 ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ቀንን አስመልክቶ ያሳየችውን የችግኝ መትከል ተነሳሽነት በቀጣናው ለማስፋት ከአገራቱ ጋር እንደሚሰራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የተካሄደውን የአረንጓዴ አሻራ ቀን አስመልክቶ ዛሬ ይዞት በወጣው ጽሁፍ ኢትዮጵያ የዛፍ ጭፍጨፋንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በአስደናቂ ሁኔታ ተክላለች ብሏል። መርሃ-ግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሃሳብ መሆኑን የሚያወሳው የድርጅቱ ጽሁፍ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ያለመ እንደነበረም አስታውሷል። በዕለቱ በ12 ሰዓታት ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር በ2016 በህንድ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻሏን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያን በመጥቀስ አስቀምጧል። የአረንጓዴ አሻራ ቀን መርሃ-ግብር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ መርሃ-ግብር፣ ከኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በታዛቢነት መገኘታቸውንም አስፍሯል። ለዓለም ስጋት እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ዛፍ መትከል ውጤታማ አማራጭ መሆኑን አውስቷል። ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ያደረገችውን ችግኝ የመትከል ዘመቻ የሚበረታታ በመሆኑ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም መሰል ተግባራትን በማከናወን ተጽዕኖውን መቋቋም እንዳለባቸው በአፍሪካ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጉዳዮች ዳሬክተር ጁሊቲ ባኦ አስገንዝበዋል። በቀጣይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑንም አንስተዋል። በዚህም የአፍሪካ አገራት ለሚያከናውኑት ተግባር የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ መርሃ-ግብር የአቅም ግንባታ ድጋፎችን በማድረግ ቀዳሚ ድርሻ እንደሚይዝ ነው የተናገሩት። ዛፍ ለስነ-ምህዳር ዘርፈ-ብዙ አገልግሎቶች ከመስጠቱ ባለፈ ለመሬትና አጠቃላይ ለአካባቢያዊ ሁኔታ ያለው ጠቀሜታ በርካታ ነው ሲሉ ይዘረዝራሉ። ዛፍ መትከል በሰው ልጅ እንቅስቃሴ አማካኝነት የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ ሁለት ሶስተኛውን ማስወደግ እንደሚችል በሳይንሳዊ መጽሄት ላይ የታተመ ጽሁፍን ጠቅሶ ተመድ በሃተታው አስፍሯል። አጥኚዎች እንደሚሉት ከሆነ አሁን ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሄክታር የዛፍ ሽፋን ያስፈጋታል። በመሆኑም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ዛፍ መትከል ትልቁና ዝቅተኛ ዋጋ የሚያስወጣ መሆኑን ድርጅቱ ያስቀምጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ብዛት ያላቸው የዛፍ ችግኞችን የመትከል ዘመቻ ውስጥ እንደሚገኙ በመጠቆም ኬንያ የጀመረችውን ”አረንጓዴ ኬንያ ኢንሼቲቭ” ኢትዮጵያ እያከናወነችው ካለው በተጨማሪ ለአብነት አንስቷል። በመሆኑም መሰል መርሃ-ግብሮችን ለማስፋፋትና የደን መጨፍጨፍን በማስቆም ሽፋኑን ለመጨመር በአህጉሪቱ ከሚገኙ አገራት ጋር እንደሚሰራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል። ድርጅቱ በ2000 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት 35 በመቶ ወደ 4 በመቶ ዝቅ ብሎ ነበር። ከተጠቀሰው ዓመት በኋላ የደን ሽፋንን ለማሳደግ መንግስት በወሰዳቸው የተለዩ እርምጃዎች በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከ15 በመቶ በላይ መድረሱን የአካባቢ፣ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም