ቀጥታ፡

በሳዑዲ እስር ቤቶችና ያለ ህጋዊ ሰነድ ይኖሩ የነበሩ 553 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመለሱ

ሐምሌ 26/2011 በሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች እንዲሁም ያለ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ በአገሪቷ ይኖሩ የነበሩ 553 ዜጎች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ትናንት ሌሊት ወደ አገራቸው የተመለሱት 280 ኢትዮጵያዊያን በሳዑዲ ዓረቢያ ጂዛን ግዛት ኢዋ እና ሲጂንነዓም እስር ቤቶች ታስረው የነበሩ ናቸው። ኢትዮጵያዊያኑ ከ5-30 ዓመት እስር የተፈረደባቸው ሲሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ጂዳ በሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ በኩል የሳዑዲ መንግስት ምህረት እንዲያደርግላቸው በተደረሰ ስምምነት ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። በተመሳሳይ በጂዳ እና ጂዛን ግዛት ያለ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ይኖሩ የነበሩ 273 ኢትዮጵያዊያን ከትናንት በስትያ ሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ከተመላሾቹ መካከል 75ቱ ሴቶች ናቸው። ኢትዮጵያዊያኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮንሱላር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አቶ ዮሃንስ ሾዴ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተቀብለዋቸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተለያዩ አገራት በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በማስፈታት፤ በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩትንም በፈቃደኝነት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም