የምሥራቅ ኢትዮጵያን አጎራባች ክልሎች ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የጸጥታ ኃይል አመራሮች ጥረት መጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የምሥራቅ ኢትዮጵያን አጎራባች ክልሎች ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የጸጥታ ኃይል አመራሮች ጥረት መጠናከር አለበት
ሐረር 26 / 2011 የምሥራቅ ኢትዮጵያን አጎራባች ክልሎች ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የጸጥታ ኃይሎች አመራሮች ጥረታቸውን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ አመለከቱ። የምሥራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች የጸጥታ ምክር ቤት የምክክርና የሰላም መድረክ ትናንት በሐረር ተካሂዷል። ዋና አዛዡ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ በላይ በመድረኩ ላይ እንዳስገነዘቡት በቀጠናው የተመዘገበውን አንጻራዊ ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የጸጥታ ኃይሎች አመራር አካላት በዕቅድ፣ በቅንጅትና በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ። ምክር ቤቱ አደረጃጀቱን እስከ ቀበሌ ድረስ በማውረድና ሕዝቡን በባለቤትነት ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የጸጥታ ኃይሎችን አቅም ለማጎልበት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ አሳስበዋል። የጸጥታ ኃይሎችና አመራር አካላት ግጭቶችን ከመከላከል ውጭ በሌሎች ተግባራት መሰማራት እንደሌለባቸው ያሳሰቡት ዋና አዛዡ፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት ራስን ማጽዳትና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ሊተኮርባቸው ይገባል ብለዋል። በክልሎቹ ለሚከሰቱ ግጭቶች ዋነኛ መንስዔዎች ኮንትሮባንድ፣ሕገ ወጥ ስደት፣ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችና የገንዘብ ዝውውርን የጸጥታ ኃይሎች በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ በመንቀሳቀስ እንዲከላከሏቸው አስገንዝበዋል። በክልሎቹ ሰላም በማስፈን የጸጥታ አካላት፣የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ወጣቶችና ማህበረሰቡ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ዋና አዛዡ መስክረዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች የክልሎቹን ሰላም አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ፣የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ለመታደግ፣የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣የጸጥታና የሰላም ሥራዎችን በኅብረተሰቡ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ባወጡት የአቋም መግለጫ አረጋግጠዋል። በመድረኩ የሶማሌ፣የአፋር፣የአፋር፣የኦሮሚያና የሐረሪ ክልሎችና የድሬዳዋ አስተዳደር ተወካዮች፣የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል የጸጥታ አመራር አካላት ተሳትፈዋል።