ሳዑዲ ሴት ዜጎቿ የወንዶችን ፈቃድ ሳይጠይቁ በነጻነት የውጭ ጉዞ እንዲያደርጉ ፈቀደች - ኢዜአ አማርኛ
ሳዑዲ ሴት ዜጎቿ የወንዶችን ፈቃድ ሳይጠይቁ በነጻነት የውጭ ጉዞ እንዲያደርጉ ፈቀደች
ሀምሌ 26/2011 ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ብቻቸውን በነጻነት ወደ የትኛውም አካባቢ እንዲንቀሳቀሱ ተፈቅዶላቸዋል። አዲስ በወጣው ንጉሣዊ አዋጅ መሰረት እድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች የጉዞ ሰነድ ለማውጣት ከወንድ ጠባቂዎቻቸው ፈቃድ ሳይጠይቁ ብቻቸውን ሄደው ማስፈፀም ይችላሉ። እንደ ፓስፖርት ያሉ የጉዞ ሰነዶችን ለማውጣት ለወንዶች የተሰጠው ነጻነት ለሴቶችም ብቻቸውን እንዲያስፈፅሙ ተወስኗል። ሴቶች የልጆቻቸውን ልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ ወሳኝ ኩነት ምዝገባዎችን ያለ አጃቢና ወንዶችን ሳያስፈቅዱ በራሳቸው ጊዜ በነጻነት እንዲያከናውኑ ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል። በአዲሱ ንጉሣዊ ውሳኔ መሰረት ሁሉም ዜጎች ጾታን፣ የአካል ጉዳትን እና እድሜን መነሻ ያደረገ አድልዖ ሳይፈፀምባቸው እኩል እንዲሰሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። የሳዑዲ ሴቶች ከዚህ ቀደም ወደ ውጭ ሀገር ለመጓዝ ወይም ፓስፖርት ለማውጣት፣ ከባሎቻቸው፣ ከአባታቸው፣ ወይም ከሌሎች ወንድ ዘመዶቻቸው ከሆኑ ጠባቂና አጃቢዎቻቸው ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸው ነበር። ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሳልማን ሴት የሳዑዲ ዜጋዎች የተጣሉባቸው ገደቦች እንዲነሱ እያደረጉ ነው። ለአብነትም ከዚህ ቀደም ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ ተፈቅዶላቸዋል። ልዑል አልጋ ወራሹ የሴቶችን የሰራተኛ ኃይል ምጣኔ 22 በመቶ ወደ 30 በመቶ በማሳደግ በ2030 የሀገሪቱን የኢኮኖሚ የመለወጥ ግብ በፈረንጆቹ 2016 ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። (ቢቢሲ)