በትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስፈን የመደማመጥ ባህል ሊዳብር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስፈን የመደማመጥ ባህል ሊዳብር ይገባል
ሐምሌ 25/20111 በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስፈን በተማሪዎች መካከል የመደማመጥ ባህልን ማጎልበት እንደሚገባ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲው የነበረው የአለመረጋጋት ችግር ተፈትቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲገባ በማድረግ በኩል የተማሪዎች አስተዋጾ የጎላ እንደነበረም ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመራቂ ተማሪዎች እንዳሉት በዘንድሮው ዓመት በጸጥታ ችግር ምክንያት በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ስራው ተስተጓጉሎ ነበር። በተማሪዎች ዘንድ የመደማመጥና በምክንያት የማመን ባህል እየጎለበተ መምጣቱ ችግሩን ፈጥኖ በመፍታት ወደ ተረጋጋና ፍጹም ሰላማዊ ወደሆነ የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ለመግባት ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሃይድሮሊክስና የውሃ ሀብት ምህንድስና ተመራቂ ተማሪ ተስፋማርያም ገብሬ ዘንድሮ የመማር ማስተማር ሂደቱ ከመስተጓጎል አንስቶ ፍጹም ሰላማዊ እስከሆነበት ድረስ ሁለት ተቃራኒ ገጽታዎች መስተናገዳቸውን ይናገራል። ተማሪው ከግጭት ትርፍ እንደማይገኝ መረዳት መቻሉ እንዲሁም የመደማመጥ ባህል እየጎለበተ መምጣት በዩኒቨርሲቲው ለመጣው ለውጥ የጎላ አስተዋጽኦ እንደነበራቸውም አመልክቷል። ከሒሳብ ትምህርት ክፍል የተመረቀችው አፍረገነት ተክሉ በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት ውጤታቸው ላይ ጫና ከማሳደሩ ባለፈ ትምህርት እስከማቋረጥ የደረሰ ችግር ፈጥሮባቸው እንደነበር አስታውሳለች፡፡ ምንም እንኳ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ ቢያልፍም የግቢው ማህበረሰብ በተለይም ተማሪው ከነበረው ችግር ተምሮ ሁለተኛውን መንፈቅ ዓመት በሰላማዊ ሁኔታ በመማር ለምረቃ መድረሳቸውን ተናግራለች፡፡ እንደተመራቂዋ ገለጻ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በዘላቂነት ማረጋገጥ ከተፈለገ በተማሪዎች መካከል የመደማመጥ ባህል ለማጎልበት በትኩረት መስራት ይገባል፡፡ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶከተር ጫላ ዋታ በበኩላቸው የ2011 የትምህርት ዘመን በስኬት እንዲጠናቀቅ በበቂ ቅድመ ዝግጅት ተማሪዎችን መቀበላቸውን አስታውሰዋል፡፡ በመጀመሪያዎቹ 6 ወራት በዩኒቨርሲቲው ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ለ5 ተከታታይ ሳምንታት የመማር ማስተማር ስራው መስተጓጎሉን ገልጸዋል። “ችግሩን ለመፍታት የአጭር ጊዜ ዕቅድ በማውጣትና የቅርብ ክትትል በማድረግ ፈጥኖ ሁኔታውን መቀየር ተችሏል” ብለዋል። እንደ ዶክተር ጫላ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው ካለመረጋጋት ተላቆ ሰለማዊ የመማር ማስተማሪ ሂደት ውስጥ እንዲገባ በተማሪው ዘንድ በንግግር የማመንና የመደማመጥ ባህል እየጎለበተ መምጣት የጎላ አስተዋጽኦ አድርጓል። ተማሪዎችን ጨምሮ ሙሉ የግቢው ማህበረሰብ ተቀራርቦ በመስራቱ የባከኑ የትምህርት ጊዜያትን ማካካስ መቻሉን ተናግረዋል። በመጪው ቅዳሜ ዩኒቨርሲቲው ከ2 ሺህ 8 መቶ በላይ ተማሪዎችን ለማስመረቅ ዝግጅት በመድረግ ላይ መሆኑንም ዶክተር ጫላ አመልክተዋል። ዩኒቨርሲቲው ከቡሌ ሆራ ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት የተመራቂ ቤተሰብ እንግዶችን ለመቀበልና ከስጋት ነጻ እንዲሆኑ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ከ13 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡