የደን ልማት በገዳ ስርአት

222
ምናሴ ያደሳ(ኢዜአ) የኦሮሞ ገዳ ስርአት በአስተዳደራዊ: ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ህዝቡ ሊመራባቸውና ሊከተላቸው የሚገባ በርካታ እሴቶች አሉት ። ስርአቱ አንድ ልጅ ተወልዶ በዚች ምድር ላይ በሚኖረው ቆይታ በስምንት አመታት ልዩነት የእድሜ ክፍፍል ፣ ስያሜና ማህበራዊ ሀላፊነቶች ይኖሩታል። በእድሜ ክፍፍሉም እስከ 8አመት ያለ ህፃን ከእናቱ ሳይለይ ተገቢውን እንክብካቤ ይደረግለታል ። ፍቅርና እንክብካቤ እያገኘም ያድጋል። በዚህ ዕድሜ ክልል ያሉ ህፃናት Dabballe(ደበሌ) ተብለው ይጠራሉ። ከ8 አመት እስከ 16 ዓመት ባለው ጊዜ ደግሞ ከእናቱ ጉያ ወጥቶ አካባቢውን እንዲላመድ ይደረጋል። አካባቢውን የሚላመድበትና በተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች መሳተፍ የሚጀምርበት ዕድሜ ነው ። ከታላላቁቹ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚማርበት የዕድሜ ክልል ነው ። በዚህ ዕድሜ ያሉ ህፃናት Gaammee Xiqqoo (ጋሜ ጢቆ)ይባላሉ ። ከ16 ዓመት እስከ 24 አመት ድረስም የተለያዩ ማህበራዊ ሀላፊነቶችን ለመቀበል የተግባር ልምምድ የሚያደርግበት ዕድሜ ነው ። የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ለመሳተፍ ስልጠና የሚወስዱበት ዕድሜ ጭምር ነው ። እነዚህ ታዳጊዎች የህብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅ የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠና ይወስዳሉ ። በእርሻ ስራዎችም መሰማራት ይጀምራሉ ።በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ወጣት Gaammee Guddoo (ጋሜ ጉዶ)ይባላል። ከ25 እስከ 32 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ሲገቡም kuusaa (ኩሳ) ተብለው ይጠራሉ ። በዚህ ዕድሜ ክልል ቀደም ሲል የወሰዱትን ስልጠና በተግባር እንዲያውሉ ሀላፊነት ይረከባሉ ። ሀገር የመጠበቅ ሀላፊነት የሚረከቡት በዚህ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ናቸው ። ከዚህም ጎን ለጎን የገዳ ስርዓት ህግጋትና አስተምህሮዎችን አውቀው ለቀጣዩ ሀላፊነት ራሳቸውን ያዘጋጃሉ:: በገዳ ስርአት አንድ ሰው ለአስተዳደራዊ ሀላፊነቶች ብቁ የሚያደርጉትን ስራዎች ለማከናወን የስርአቱን እሴቶች እና ህግጋት የሚማርና የሚለማመደው ደግሞ ከ32 እስከ 40 አመቱ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው ። በጦር መሪነት ከመመረጥ አንስቶ በአባ ገዳ፣ አባ ዱላ አባቃሉ ፣ አባ ሴራና ሌሎች አመራሮች የሚሰጡትን አስተዳደራዊ ስራዎች መከወን ይጀምራል ። ይህ የዕድሜ ገደብ አንድ ሰው ስለ ስርአቱ ባለው ዕውቀትና አፈፃፀም ተገምግሞ ለአባ ገዳነት የሚታጭበት ዕድሜ ነው ። በዚህ የዕድሜ ገደብ የሚገኙ ሰዎችም Rabaa Doori (ረባ ዶሪ) ተብለው ይጠራሉ:: በስርአቱ አንድ ሰው ለገዳ አመራርነት ብቁ መሆኑ ተመዝኖ የሚመረጠውም እድሜው 40 አመት ሲሞላው ነው ። በዚህ ዕድሜ ብቁ ሆኖ ለገዳ አመራር የተመረጠ ሰውም የስልጣን ዘመኑ ስምንት አመት ብቻ በመሆኑ በ48 አመቱ ስልጣኑን ለተተኪው ያስተላልፋል ። በህይወት እስካለ ድረስም በየስምንት አመቱ በሚከፋፈል የተለያዩ ስራዎች ይመደባል ። ይሄውም የአማካሪነት የአስታራቂነትና የድጋፍ ሰጪ ሀላፊነቶች ይኖሩታል። የገዳ ስርአት በአስተዳደራዊ: ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ዘርዘር ያሉ ህግጋት አሉት ። እያንዳንዱ ሰው የሚጠበቅበትን ግዴታና የሚኖሩትን መብቶች ያስቀምጣል። በገዳ ስርአት ከተደነገጉትና በማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ያተኮሩ ድንጋጌዎች ውስጥ ለዛሬ ደን ፣ ዛፎችና እንስሳትን በተመለከተ ያሉትን እንመልከት ። የገዳ ስርአት ከደነገጋቸው ግዴታዎችና መብቶች አንዱ የዕፅዋትና እንስሳት መብት የተመለከተ ነው ። በገዳ ስርአት በተለይ ለዛፎችና በውስጡ ለሚኖሩ የዱር እንስሳት ተገቢው ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲደረግ ግዴታ ተቀምጧል ። የሰው ልጅ ዛፎችንና በውስጡ የሚገኙ እንስሳትን ተገቢ በሆነ ሁኔታ መጠቀም ቢችልም በዘፈቀደና ለጥፋት በሚዳርግ መልኩ ጉዳት ማድረስ የተከለከለ ነው ። በኢሉአባቦር የሰግለን ኢሉ አባገዳ ከሊፋ ሾኖ እንዳሉት የገዳ ስርአት ለሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ ለደን ፣ለዛፎችና በውስጣቸው ለሚኖሩ የዱር እንስሳት ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግ ያስገድዳል ። ለደንና ለዛፎች የሚሰጠውን ትኩረት የሚጀምረው ማንኛውም ሰው ወደ ደን ክልል ከመግባቱ በፊት ስለ አጠቃቀሙ በቂ ዕውቀት ሊኖረው እንደሚገባ ከማስገደድ ይጀምራል" ይላሉ:: በስርዓቱ ማንኛውም ሰው በደን ውስጥ የሚገኙ ዛፎችን ለቤት መስሪያ: ለማገዶ እና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ለመጠቀም ከዚህ በታች ያሉትን መመሪያዎች መከተል ይጠበቅበታል:: የእድገት ዘመናቸውን ከጨረሱ ትላልቅ ዛፎች ቅርንጫፎች በመቁረጥ:: - ከዛፎቹ ውስጥ በመምረጥ የደረቁትን ብቻ መቁረጥ - የቅጠል አይነታቸው ወይም መጠናቸው ለአየር ንብረት ጠቀሜታቸው እምብዛም ያልሆኑትን ብቻ በመምረጥ መቁረጥ ግዴታ ነው ። በገዳ ስርአት ከተደነገጉት አስገዳጅ መመሪያዎች ውጪ ለአየር ንብረት ፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለኢኮኖሚው ፋይዳ ያላቸውን ዛፎች በዘፈቀደ መቁረጥ ለከባድ ቅጣት የሚዳርግ መሆኑን ነው አባ ገዳው የገለፁት ። በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ዛፎቹ ከተቆረጡም የቆረጠው አካል በምትካቸው ችግኞችን በመትከል ፀድቀው ሙሉ ዛፍ እስኪሆኑ ድረስ የመንከባከብ ግዴታ እንዳለበት ተቀምጧል ። አባገዳው እንዳሉት በገዳ ስርአት ዛፎች ያላቸውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት ህብረተሰቡ ችግኞችን በየወቅቱ ተክሎ እንዲንከባከብ ትምህርቶች ይሰጣሉ ። ለአየር ንብረት ለውጥ፣ የአፈር መሽርሸርን ለመከላከል ፣ የወንዞች መጠን እንዲጨምርና በመሳሰሉት መስኮች ላይ ያለውን የደን ጠቀሜታ በገዳ ስርአት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረጉን ነው አባገዳው የሚናገሩት ። የደን መኖር ለሰው ልጅ ካለው ጠቀሜታ ባሻገር ለእንስሳት ጤናማ ህይወትም ጠቀሜታ አለው ። በተለይ በደን ክልል ብቻ መልማት የሚችሉ የቅመማ ቅመም ሰብሎች እና ቡና ደን ከሌለ መጥፋታቸው አያጠያይቅም ። አባገዳ ከሊፋ ሾኖ እንደነገሩኝ በተለይ በኢሉአባቦር ዞን ከ168 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚገኘው የተፈጥሮ ጥቅጥቅ ደን ከአለም ቅርሶች አንዱ ተደርጎ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት:ባህልና ሳይንስ ማዕከል(ዩኒስኮ) መመዝገቡ የአካባቢው ማህበረሰብ በገዳ ስርአት አስተምህሮት ደኑን ጠብቆ በማቆየቱ ነው ። ይህ የገዳ ስርዓት አስተምህሮት አካባቢው ለረጅም ዘመናት በደን እንዲሸፈን ከማድረጉም ባሻገር ከደለል ነፃ ሆነው ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞችም ከአመት አመት መጠናቸው እንዳይቀንስ አድርጓል ። የሰግለን ኢሉ አባገዳዎች ጉባኤ አባል አባገዳ ሀይሉ ለገሰ ቤኮም በበኩላቸው የደን ዛፎችና በውስጣቸው የሚገኙ የዱር እንስሳት ሊደረግላቸው ስለሚገባ ጥበቃና እንክብካቤ የገዳ ስርአት አስተምህሮዎችን እንደሚከተለው ነግረውኛል ። የደን መኖር ከሰው ልጅ በህይወት መኖር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ስርአቱ ያስተምራል ። የደን ዝርያ እንዳይመናመን ህብረተሰቡ በበጋ ወቅት አፍርተው የሚረግፉ የዛፍ ዝርያዎችን ለቅሞ እንዲያከማች ትምህርት ይሰጣል ። የተለቀሙት የዛፍ ፍሬዎችም ፈልተው ተዘጋጅተው በየአመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር ደን በሳሳበትና በተራቆቱ አካባቢዎች ይተከላሉ ። በተለይ የገዳ ስርአት እንደሚያስተምረው ድርቀት የማያስከትሉና የአፈር መሸርሸርን በደምብ የሚከላከሉ የዛፍ አይነቶች በወንዞች ዳርቻ ግራና ቀኝ እንዲተከሉ ስርአቱ ያዛል ። አባገዳው እንዳሉት ይህም በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች አሉት ። ከእነዚህ ጠቀሜታዎቹ መካከል አፈር ተሸርሽሮ ወደ ወንዞች እንዳይገባና በደለል እንዳይሞላ መከላከል አንዱ ነው ። የወንዞች መጠን ሳይቀንስ ክረምት ከበጋ በእኩል እንዲፈስና ከአፈርና የተለያዩ ቆሻሻዎች በፀዳ መልኩ እንዲፈሱ ለማድረግ ነው ። አባገዳ ሀይሉ እንደነገሩኝ የኦሮሞ ገዳ ስርአት ለዛፎችና ለደን ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ በውስጡ ለሚኖሩት የዱር እንስሳት ጥበቃ እንዲደረግ ይደነግጋል ። ስርአቱ እንደሚያዘው በአደንና በማናቸው ምክንያቶች ታዳጊ የዱር እንስሳት መግደል የተከለከለ ነው ። ሴት የዱር እንስሳት ደግሞ ፈፅሞ መግደል አይፈቀድም ። ይህም ዝርያቸው እንዳይጠፋ እና እንዳይመናመን በማሳብ ነው ። አባገዳዎቹ እንዳሉኝ ሰሞኑን በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በአንድ ቀን ከ200 ሚሊዮን በላይ የዛፍ ችግኞች ለመትከል ታቅዶ የተፈጠረው ህዝባዊ ንቅናቄ በእጅጉ የሚደነቅ ተግባር ነው ። የሰግለን ኢሉ አባገዳ ከሊፋ ሾኖ እንዳሉት የደን ጠቀሜታ በአንድ በኩል ብቻ የሚታይ ሳይሆን ከሁሉም የሰው ልጆች ፍላጎቶች ጋር የተያያዘ በመሆኑ በችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ በየግዜው ለህብረተሰቡ ትምህርት እየሰጡ ነው ። ደን ከሁሉም የልማት ዘርፎች ጋር በእጅጉ የተያያዘ በመሆኑ ህብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ያሳየውን ተነሳሽነት ክረምት በመጣ ቁጥር በማስታወስ የዛፍ ችግኞችን ተክሎ እንዲንከባከብ መክረዋል ። በገዳ ስርአት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የደን ጥበቃና እንክብካቤ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ቢተገበር የደን መጠናችንን ወደ ነበረበት ከመመለስ ባለፈ የውሀ ሀብታችንን በመጠቀም ለጀመርነው ትላልቅ የሀይል ማመንጫዎች ውጤታማነት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ። በተለይ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የታየው አመርቂ ውጤት ህብረተሰቡ ብቁ አመራር ካገኘ ሀገሪቱን ለመለወጥ ከፍተኛ ተነሳሽነት ያለው መሆኑ የታየበት ነው ። ይህ አይነቱ ተግባር በመላው የሀገሪቱ ህዝቦች ሰፊ ተሳትፎ መከናወኑ ደግሞ ህብረተሰቡ ስለ ደን እና አካባቢ ጥበቃ ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን ያሳያል:: በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ሀገሪቱ ያከናወነችው ተግባር ሰፊውን የሰው ሀብቷን በመጠቀም በሌሎች የልማት መስኮችም ሪከርድ መስበር እንደምትችል ያረጋገጠ አቅም መኖሩን አሳይቶናል ። እናም አቅማችንን በሁሉም የልማትና የሰላም መስኮች እንጠቀምበት ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም