በአማራ ክልል ሻዳይ ፣ አሸንድዬና ሶለል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሻዳይ ፣ አሸንድዬና ሶለል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው
ሀምሌ 25/2011 በአማራ ክልል በየዓመቱ የሚከበረውን የሻዳይ፣ አሸንድየና ሶለል የልጃገረዶች በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጀመሩን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ አቶ ግዛት አብዩ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ኃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያለው የሻዳይ፣ አሸንድየና ሶለል በዓል የአማራ ህዝብ የማንነት መገለጫና የኢትዮጵያዊያን የባህል ሃብት ነው። ሆኖም እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ትኩረት ሳይሰጠው ረጅም ዘመናትን አሳልፏል። "በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ቀን እስከ ነሐሴ 20 ባሉት ቀናት የሚከበረው በዓሉ ከኃይማኖታዊና ባህላዊ ፋይዳዊ በተጨማሪ ሴቶች ለነጻነትና ለእኩልነት እንዲታገሉ ተምሳሌታዊ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው" ብለዋል ። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለዘመናት በድምቀት ሲከበር የነበረው ይኽው በዓል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚከናወነው በሁለት ዞኖች ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዋግኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሻዳይ፣ በሰሜን ወሎ ዞን በላስታ ላሊበላ ወረዳ አሸንድየ፣ በቆቦ ወረዳ ደግሞ ሶለል በሚል ስያሜ በዓሉን ልጃገረዶች በአደባባይ በመውጣት ያከብሩታል። በዓሉ ኃይማኖታዊ ትርጉም ያለውና የሴቶችን መብትና እኩልነትን የሚያረጋግጥ ጭምር እንደሆነ የቢሮው ኃላፉ አስረድተዋል። በዓሉ እንደ ክልል ባለፈው ዓመት በድምቀት ማክበር የተጀመረ መሆኑን ጠቁመው ዘንድሮ በሁሉም የክልሉ ዞኖች ለማክበር የቅስቀሳ ኮሜቴ እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ተፈጥረው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። ኃላፊው እንዳሉት ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 18 በዞኖችና ወረዳዎች ፣ ነሔሴ 19 እና 20 ደግሞ በክልል ደረጃ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት ባህር ዳር ከተማ ላይ በድምቀት ይከበራል። ባህል የአንድ ህዝብ መገለጫ በመሆኑ ሳይበረዝና ሳይከለስ ለትውልድ ለማስተላለፍ ህዝቡ ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል። ከአማራ ክልል ባለፈ በትግራይ ክልልም የሚከበር እንደመሆኑ " የኢትዮጵያ ልጃገረዶች በዓል” በሚል እንደ ሀገር በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ባህልና ሳይንስ ደርጅት(በዩኔስኮ ) በቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ተሟልተው መዘጋጀታቸውም ተገልጿል። ለዚህም የተጀመረው እንቅስቃሴ እውን እንዲሆን ህዝባዊነቱ መጉላት እንዳለበት ፣ህዝቡ በድምቀት ሊያከብረውና ሊንከባከበው እንደሚገባ ተመልክቷል።