የማዕድን ኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥን ለማዘመን የሚያስችል አዲስ ድረ ገፅ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድን ኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥን ለማዘመን የሚያስችል አዲስ ድረ ገፅ ይፋ ሆነ
ኢዜአ ሀምሌ 25 2011 የኢትዮጵያ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ ስረዓትን ለማዘመን የሚያስችል አዲስ ድረ ገፅ ይፋ አደረገ። ድረ ገፁ "ላንድፎሊዮ የካዳስተር" የሚባል ሲሆን፤ አገሪቷ በዘርፉ ያላትን ሃብት፣ የሚገኝበትን አካባቢና በባለሀብቶች ጥያቄ የቀረበበት መሆኑና መያዙን ካሉበት ቦታ ሆኖ መረጃውን በማየት ማረጋገጥ ያስችላል። በመሆኑም በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ኩባንያዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ሙሉ መረጃ እንዲኖራቸውና በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው ፈቃድ መጠየቅ፣ ያሰደሱበትን መረጃና አስፈላጊ የክፍያ ሰነዶችን በድረ-ገፁ ላይ በመጫን ለሚመለከው እንዲደርስ ማድረግ ያስችላል። የኢትዮጵያ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰፋ ኩምሳ በመርሃግብሩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት "ላንድፎሊዮ የካዳስተር "የተባለው ይህ ድረ ገፅ ባለሀብቶች ከአሁን በፊት በአካል ለመገኘት የሚያወጡትን ገንዘብና ጊዜ የሚያድን ነው። አመልካቾች ከሰራተኛው ጋር በአካል ስለማይገናኙ ሊፈጠሩ የሚችሉ የመልካም አስተዳደርና ቢሮክራሲያዊ ችግሮችንም ይቀንሳል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም አገሪቷ ያላትን የማዕድን ሃብትም ለአለም ከማስተዋወቅ አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በድረ ገፁ ላይ የተለያዩ የማዕድን መረጃዎች እየተጫኑ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አስፈላጊ መረጃዎች በሙሉ ተጭነው እስከ ህዳር ድረስ ስራ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጀምር ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አሁንም እየገቡ አንዳንድ መረጃዎችን መጎብኘት እንደሚቻልም ታውቋል። ከአሁን በፊት ዘርፉ ይጠቀምበት የነበረው አሰራር "ፍሌክሲ ካዳስተር" የተሰኘ ሲሆን፤ ፈቃድ አመልካቾች አስፈላጊ መረጃዎችን በአካል ቀርበው ማምጣት ይጠበቅባቸው ነበር። በአገሪቷ ውስጥ ያሉ የማዕድን ዓይነቶችንና ቦታዎችን፣ እንዲሁም በሌሎች ባለ ሃብቶች መያዝ አለመያዛቸውንም በግልፅ ለማሳየት አያስችልም። ድረ ገፁን ለመጎብኘት https://ethiopian.portal.miningcadastre.com በሚለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል።