ቀጥታ፡

ጃፓን ለኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ድጋፍና አጋርነቷን እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ገለጹ

ሀምሌ 25/2011 በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኪ ማቱሱንጋ እና የኢምባሲው ሰራተኞች የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ በመደገፍ በኢምባሲው ቅጥር ግቢ ችግኝ ተከሉ። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኪ ማቱሱንጋ በእለቱ እንደተናገሩት አገራቸው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓደ ልማት መርሃ ግብር አገራቸው ትደግፋለች። በኢምባሲው ቅጥር ግቢ የተከናወነው ችግኝ ተከላም ይህንኑ አላማ የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል። አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን  በመትከል የአለምን ክብረ ወሰን በመስበሯ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። የተተከሉት ችግኞች ከጸደቁና እንክብካቤ ካገኙ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ  ሚስተዋለውን  አየር ንብረት መዛባት በማስተካከል ሂደት ጉልህ ሚና እንደሚኖራትም አስረድተዋል። ሌሎች የአለም አገራትም የኢትዮጵያን ፈለግ በመከተል በአረንጓዴ ልማት የድርሻቸውን ቢወጡ በዓለም ላይ እየታየ ያለውን የአየር መዛባት ማስተካከል ይቻላል ብለዋል። ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነችው ያለው ልማት በአርአያነት የሚጠቀስ በመሆኑ  አገራቸው የምትደግፈው ተግባር መሆኑንም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት የኢምባሲው ሰራተኞች መካከል አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኞቹን ተንከባክበው ለማሳደግ ተዘጋጅተዋል። ኢትዮጵያና ጃፓን ከ85 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም