ምክር ቤቱ የተለያዩ አዋጆችን በማፅደቅ ተግባራዊነታቸውንም ክትትል ማድረጉን አስታወቀ

62
ሐምሌ 25 / 2011ኢዜአ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባለፍው አንድ ዓመት አምስት የተለያዩ አዋጆችን በማፅደቅ ለተግባራዊነታቸውም በቋሚ ኮሚቴዎች ክትትል ማድረጉን አስታወቀ። ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ ለ42 ተቋማት የክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ ሥራ ማከናወኑም ታውቋል። የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በምክር ቤቱን የ6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ባለፈው በጀት ዓመት አምስት የተለያዩ አዋጆች መፅደቃቸውን ገልጸዋል። የፀደቁት አዋጆች የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውንም አስታውሰዋል። ለአዋጁ የማስፈጸሚያ ደንብ በማዘጋጀት ለዚሁ ሥራ በተደራጀ ክፍል አማካኝነት የሥርጸት ሥራ መሠራቱንም አስረድተዋል። የወጡት አዋጆች በአግባቡ እየተተገበሩ ለመሆናቸው በቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት ክትትል መደረጉንም አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል። ምክር ቤቱ ለ42 ተቋማት የክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ ሥራ ማከናወን ችሏል። በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ቋሚ ኮሚቴው ከአስፈጻሚው ጋር በተፈራረመው የዕቅድ ግብ ውል ስምምነት መሠረት መከናወኑንም ወይዘሮ አበበች ገልጸዋል። በዚህም መሰረት በቋሚ ኮሚቴዎች ከተመዘኑት 42 ተቋማት መካከል 6ቱ በጥሩ አፈፃፀም፣ 31 መካከለኛ እና ቀጣይ ክትትልና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 5 ተቋማት ተለይተዋል። በሂደቱ የሁሉንም ተቋማት የምዘና ሂደትን ጨምሮ 4 ጊዜ የሱፐር ቪዥንና ድንገተኛ የመስክ ምልከታ ሥራ መከናወኑንም ጠቅሰዋል። አሠራሩ በክፍለ ከተማና በወረዳ ምክር ቤቶች ደረጃም እንዲወርድ በማድረግ የኅብረተሰቡን አገልግሎት አሰጣጥና ፍትሃዊ ተጠቀሚነት ከፍ ለማድረግ ክትትል፣ ቁጥጥርና የድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱንም ወ/ሮ አበበች ተናግረዋል። ከሁሉም ክፍለ ከተማ ከተወጣጡ ከ3 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር አመራሩ ባደረገው ውይይት ሲነሱ በነበሩ የመኖሪያ ቤት ችግር፣የሰላም፣የልማት፣የኑሮ ውድነት፣የሥራ ዕድል ፈጠራ፣የትራንስፖርት እና የሕገ ወጥ ንግድን በተመለከተ ቀጣይ ሥራዎች የሚፈልጉ ቢሆኑም መፈታት መጀመራቸውን ምክር ቤቱ ማረጋገጡን አስረድተዋል። በከተማዋ የሚስተዋሉት ሕገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የመንገድና ሌሎች ግንባታዎች መጓተትና ተቆፍረው የሚተው ጉድጓዶች በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ስለመሆኑም ከነዋሪዎች የተነሱ ጥያቄዎች መሆናቸውም ተገልጿል። በመብራት፣ በውሃ፣ በትምህርት ጥራትና በግል ትምህርት ቤቶች ያለምክንያት ዋጋ ጭማሪ ላይ የተነሱ ቅሬታዎችን ምክር ቤቱ ተቀብሎ ግምገማ በማድረግ ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አፈ ጉባኤዋ አስረድተዋል። ምክር ቤቱ ባለፉት ዓመታት በኦዲት ግኝት ተይዘው ሲንከባለሉ የነበሩና ያለ አግባብ የባከኑ የመንግሥት ሃብቶች ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ በምክር ቤቱ አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ፀድቆ ወደ ተግባር የተገባው የተጠያቂነት አሠራር ወሳኔን ተግባራዊ እንዲሆን ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል። የኦዲት ግኝት የታየባቸው ተቋማት የሰጡትን ምላሽ እንዲሁም ምላሽ ባልሰጡት ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በኩል በዚህ ጉባኤ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም