የፍቼ ጫምባላላ በዓል ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ወጣቶች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የፍቼ ጫምባላላ በዓል ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ወጣቶች ተናገሩ

ሀዋሳ ሰኔ 5/2010 በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል ፍቼ ጫምባላላ ባህላዊ ስርዓቱ ጠብቆ ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ወጣቶች ተናገሩ፡፡ በዓሉ ነገ በሀዋሳ እንዲሁም በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ደግሞ ለአስራ አምስት ቀናት እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች እንደገለጹት በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር የአንድነትና የመከባበር እንደመሆኑ ስርዓቱን ጠብቆ በሰላም እንዲጠናቀቅ ይደግፋሉ፡፡ ወጣት ማቲዮስ ጃንጄ የሀዋሳ ከተማ የሚኖር የሲዳማ ተዋላጅ ሲሆን" የፍቼ ጫምባላላ በዓል የሲዳማ ብቻ አይደለም፤ የአለም ቅርስም ነው፤ የበዓሉን ትክክለኛ ገጽታ በማንጸባረቅ ዝግጅት አከብረዋለሁ" ብሏል፡፡ የማያውቀውን ስነስርዓት ከአባቶች እየጠየቀና እየተማረ ወጣቱ በዓሉን ቀጣይ ለማድረግ መስራት እንደሚገባው ጠቁሞ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመከባበር እና የመቻቻል ስርዓት ያለው መሆኑን ተናግሯል፡፡ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ኦሊቨር ግዴሳ በበኩሉ ፍቼ ጫምባላላ የሲዳማ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ብሔረሰቦች በጋራ የሚያከብሩት የአንድነትና የሰላም በዓል መሆኑን ገልጿል፡፡ የበዓሉ ስርዓት ከኢትዮጵያም አልፎ በዓለም ደረጃ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ እንደሚያኮራው ተናግሯል፡፡ ፍቼ ጫምባላላ ሰላም የሚሰበክበት በዓል እንደመሆኑ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ወጣቶቹ ገልጸዋል፡፡ የሲዳማ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ እንደገለጹት የፍቼ ጫምባላላ በዓል የክልሉና የፌዴራል አመራሮች የሲዳማ ብሔር ተወላጆችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ነገ በሀዋሳ ጉዱማሌ ይከበራል፡፡ የበዓሉ ስርዓትን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት ጥናቶች መካሄዳቸውንና እነዚህን በሰነድ አደራጅቶ ለታሪክ ለማቆየት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዓሉ ነገ በሀዋሳ እንዲሁም በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ደግሞ ለአስራ አምስት ቀናት እንደሚቀጥል አቶ ጃጎ አመልክተዋል፡፡ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ በዓል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም በማይዳሰስ የአለም ቅርስነት የተመዘገበው ህዳር 2008 ዓ.ም እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡