ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 4 ቢሊዮን ብር ካሳ ከፍሏል

አዲስ  አበባ  ሐምሌ 25/20111 ኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በ2011 በጀት ዓመት ለካሳ ክፍያ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎቹን አስመልክቶ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል  ሰጥቷል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ለወሰን ማስከበርና ለካሳ የሚፈጸመው ክፍያ የተጋነነና በመንገድ ፕሮጀክቶች በጀት ላይ የሚያሳድረው ጫናም እየጨመረ ነው። በበጀት ዓመቱ ለመንገዶች ግንባታ ከተመደበው 28 ቢሊዮን ብር ውስጥ 4 ቢሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ መዋሉን ነው የገለጹት። ይህም የግንባታዎችን ዋጋ የማናር፣ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቂያ ጊዜ የማራዘምና ሌሎች ክፍተቶችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል። እንደ ኢንጂነር ሀብታሙ ገለጻ በበጀት ዓመቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች የፊዚካል ስራዎች አፈጻጸም 63 በመቶ ነው። ከፍተኛ የፕሮጀክት ብዛትና የስራ ጫና፣ የፀጥታ ችግር፣ የግንባታ ግብዓቶች እጥረት፣ የአማካሪዎችና የስራ ተቋራጮች አቅም ክፍተት የጸጥታና ሌሎች ችግሮች ለአፈጻጸሙ ዝቅተኝነት እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል። በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው የግንዛቤና የባለቤትነት ስሜት ማነስ ሳቢያ በመንገዶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች፣ ከተፈቀደው እጥፍ ክብደት ያላቸው ተሽከርካሪዎች በመንገዶች መጓጓዝና ሌሎችም ችግሮችን አንስተዋል። የመንገድ ዘርፍ ፖለሲና አዋጅ ማዘጋጀት፣ የወሰን ማስከበር ስራዎችን አስቀድሞ መከወን፣ የምህንድስና ግዢን ቀልጣፋና ግልጽ ማድረግ፣ የባለስልጣኑን የሪፎርም ስራዎች አጠናክሮ መቀጠልና ሌሎች ተግባራት የባለስልጣኑ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል። እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በ2012 በጀት ዓመት ለመንገዶች ግንባታ 38 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። ይህ በጀት ባለስልጣኑ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለሚከናወኑ የመንገድ ግንባታዎች በመንግስት ከሚመደብ በጀት ከፍተኛውና የመንገድ ዘርፉን የሚያበረታታ እንደሆነ ነው የገለጹት። በጀቱ በ2011 በጀት ዓመት ከተያዘው ጋር ሲነጻጸርም 37 በመቶ ጭማሪ አለው። ኢንጂነር ሀብታሙ እንደተናገሩት በ2012 በጀት ዓመት 91 አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይጀመራል። ከፕሮጀክቶቹ መካከል የአዳማ-አዋሽ ፈጣን መንገድ፣ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ትስስርን የሚያጠናክሩ መንገዶች፣ የከተማ ተለዋጭና ሌሎች መንገዶችን ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቶቹ ከ150 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል። የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም ከመንገዶች ግንባታ ፍትሃዊነት፣ የመንገድ ጥራትና ጥገናና የፕሮጀክቶች መዘግየት ጋር የተያያዙ ችግሮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች አንስተዋል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በሰጡት ምላሽ ባለፉት ዓመታት በነበሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ሳቢያ የመንገዶች ግንባታ ላይ 'የፍትሃዊነት ክፍተት ሊኖር ይችላል' ብለዋል። የፕሮጀክቶች ጥራትና በወቅቱ ያለማጠናቀቅ ችግሮች በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ዘርፎች የነበረ መሆኑን ገልጸው ባለስልጣኑ እያከናወነ ባለው የለውጥ ስራ ውጤት ለማምጣት እየሰራ ነው ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም