ረቂቅ አዋጁ የዜጎችን የመምረጥና የመመረጥ መብት የሚገድብና የፓርቲዎችን ህልውና የሚጋፋ ነው - ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ አዋጁ የዜጎችን የመምረጥና የመመረጥ መብት የሚገድብና የፓርቲዎችን ህልውና የሚጋፋ ነው - ፓርቲዎች
ሀምሌ 25/2011 የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን የመምረጥና የመመረጥ መብት የሚገድብና የፓርቲዎችን ህልውና የሚጋፋ ነው አሉ ሰላሳ ሶስት የፓለቲካ ፓርቲዎች። በረቂቅ አዋጁ በፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦች አለመካተታቸውንም ነው የገለጹት። ሰላሳ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ረቂቅ አዋጁ ላይ ፓርቲዎች ስምምነት ሳያደርጉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳያጸድቀው ጠይቀዋል። የህግ ማሻሻያ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አሻሽለው ለምክር ቤቱ የቀረበው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ ይዘቱ የዜጎችን የመደራጀት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት የሚገድብና የመላውን ህዝብ ጥቅምና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ህልውና የሚጋፋ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል። በረቂቅ አዋጁ ለፓርቲዎች ምዝገባ መመዘኛነትና ለዕጩ ተወዳዳሪዎች የቀረበው መስፈርት ተቀባይነት የሌለውና የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን የሚጨፈልቅ መሆኑንም ነው የገለጹት። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከረቂቅ አዋጁ ውስጥ ሁለት አንቀፆች እንዲሰረዙና 13 ደግሞ እንዲሻሻሉ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው እነዚህ አንቀፆች ሳይሻሻሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከማጽደቅ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል። "የምርጫ ቦርድ ገለልተኛነት አጠያያቂ ነው" የሚሉት ፓርቲዎቹ በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት ሲደረግ ያቀረቧቸው የማሻሻያ ሀሳቦች አለመካተታቸውን ነው ያብራሩት። ለአብነትም አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት ቀደም ሲል አንድ ሺህ 500 አባላት ይጠየቅ የነበረ ሲሆን በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ግን የመስራች አባላት ቁጥር 10 ሺህ እንዲሆን ተደርጓል። ለክልል ፓርቲነትም ከ750 ወደ 4 ሺህ 500 ከፍ ብሏል። ይሁንና ፓርቲዎቹ በውይይት ጊዜ በዚህ ቁጥር አልተስማማንም ለአገር አቀፍ ፓርቲ ምስረታ ሶስት ሺህ አባላት ለክልላዊ ደግሞ አንድ ሺህ 500 አባላት ነው ብለዋል። ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ላይ የየትኛውንም ፓርቲ የማሻሻያ ሀሳብ ሳያካትት ለምክር ቤቱ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም ነው ያሉት። ፓርቲዎቹ የህግ ማሻሻያ ምክር ቤቱና ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረቡት ረቂቅ አዋጅ ከስምምነታቸው ውጪ በመሆኑ እንደገና በስፋት በማወያየት ፓርቲዎቹ የተስማሙበት ሀሳብ እንዲካተት ጠይቀዋል። በመሆኑም የህግ ረቂቁ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መንግስትና ገዥው ፓርቲ በተገኙበት በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደገና ለመወያየት በቂ ጊዜ ሊመደብ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በመግለጫው ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን አስተያየት ጠይቋል። የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ ረቂቅ አዋጁ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ማድረጋቸውንና ይሻሻሉ ያሏቸው ጉዳዮች ላይም ሀሳብ መስጠታቸውን ገልጸዋል። በምርጫ ህጉ ረቂቅ አዋጅ ላይ ለስምንት ወራት ያህል ጥናቶች ሲካሄዱና የፖለቲካ ፓርቲ አባላትም በጥናቱ ሲሳተፉ እንደነበርም አስታውሰዋል። ከአገር አቀፍና ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታና ተሞክሮ በመነሳትም የህግ አርቃቂ ኮሚቴው በረቂቅ አዋጁ ላይ እንዲካተቱ ማድረጉን ነው ያብራሩት። ከፖለቲካ ፓርቲዎች የመጡ ማሻሻያ ሀሳቦች መካተታቸውን በመግለጽ። ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያነሷቸው ቅሬታዎችን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በማቅረብ ከመጽደቁ በፊት ውይይት ሊደረግበት ይችላል ነው ያሉት። ከ33ቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት(ኢዴህ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ(ኦነንፓ) እና የአፋር ህዝብ ነጻነት ፓርቲ(አህነፓ) ይገኙበታል።