ቀጥታ፡

ሁለት የአምራች ኢንዱስትሪ ማህበራት ተዋሃዱ

አዲስ  አበባ  ሐምሌ  25/20111 የኢትዮጵያ የታሸገ ውሃና የለስላሳ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር እና የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ማህበር ተዋሃዱ። የኢትዮጵያ የታሸገ ውሃና የለስላሳ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዛሬ አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ ነው መዋሃዳቸው የተገለጸ። የታሸገ ውሃና የለስላሳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር የቦርድ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ጌትነት በላይ እንዳሉት ሁለቱ ማህበራት መዋሃድ ያስፈለጋቸው በግብአት፣ በሰው ሃይልና በገንዘብ ራሳቸውን አጠናክረው በጋራ ለመስራት ነው። በተጨማሪም ማህበራቱ በተናጠል ያደርጉት የነበረውን በጋራ ቢያደርጉ ያላቸውን ተሰሚነት ለመጨመር ያግዛል ብለዋል። የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ገበያው ቸኮል ባለፉት ሁለት ዓመታት የአባላት ቁጥር ማነስ፣ የቢሮና የበጀት እጥረት ማህበሩን ያጋጠሙት ችግሮች መሆናቸውን አስታውሰዋል። በዚህም  የአቅም ውስንነት እንዳጋጠመው ጠቁመው አቅማቸውን ለማጠናከር ከታሸገ ውሃና የለስላሳ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር ጋር ውህደት መፈጸማቸውን ገልጸዋል። አባላቶቻቸው ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በለስለሳ፣ በውሃና በጁስ ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማሳደግ ስራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል። የሁለቱ ማህበራት ውህደት ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኔ ገብረስላሴ ሁለቱም ኢንዱስትሪዎች ተያያዥነት ያለው የምርት ሂደት ስለሚከተሉ መዋሃዳቸው ተጠናክረው በመስራት የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ያግዛቸዋል ብለዋል። እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ማህበሩ የጥራት ቤተ-ሙከራ እንዲኖረው ለማድረግ ከዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር እየሰሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል። ማህበሩ አስመስሎ የማምረትን፣ የምርት ምልክት መስረቅ፣ አላስፈላጊ የንግድ ውድድርንና ሌሎች ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል በተጠናከረ መንገድ እንደሚሰራ ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት። በተጨማሪም ከመንግስት ጋር በመሆን የህብረተሰቡን ጤና ሊጎዱ የሚችሉና ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን ለማጋለጥ እንሰራለን ነው ያሉት። የታሸገ ውሃ፣ የለስላሳ መጠጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ ኢንዱስትር መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር ሚናው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ በቀለ መኩሪያ ናቸው። ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ እንዲሆን ወኪል ማህበራት አሰራርና አቅማቸውን በማጎልበት ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉም ጨምረዋል። በመሆኑም የተዋሃዱት ማህበራት ይህን እውን ለማድረግ፣ አባላቶች ጥራት ያለው ምርት ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡና ህገ-ወጥነትን ለመከላከል እንዲሰሩ ጠይቀዋል። በጉባኤው የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢና የቦርድ አባላት ተመርጠዋል። በኢትዮጵያ 85 የታሸገ ውሃ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ሁለት የለስላሳ አምራቾች እንደሚገኙ በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም