ቀጥታ፡

ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ገለጹ

ደሴ ኢዜአ ሐምሌ 24/2011 ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበት እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ሚስተር አልቡሽራ ባስኑር አስታወቁ። አምባሳደሩ ከደሴ ከተማ አስተዳደርና ወሎ ዩንቨርሲቲ አመራሮች ጋር በግንኙነታቸው ዙሪያ ተወያይተዋል።

በደሴ ከተማ ባደረጉት በዚህ ወይይት ወቅት አምባሳደሩ እንደገለጹት ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ዘርፎች የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን በማጎልበት ትስስራቸውን ማጠናከር ይፈልጋሉ።

የሁለቱ ሀገራት ነጋዴዎችና ባለሃብቶችን በማቆራኘት የኢንቨስትመንቱንና የቱሪዝም ፍሰቱን የሚያነቃቁ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰማሩ ኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች ለሁለቱ ሀገራት ምጣኔ ሀብት መዳበር ጉልህ ሚና መጫወት በመጀመራቸው ይህንን ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ለማስፋፋት አቅደዋል፡፡

በተለይ ደሴን ጨምሮ በወሎ ያሉ ተፈጥሮዊ የቱሪዝም ሀብቶች በአግባቡ በዘመናዊ ቴክኖሎጅ ተጠቅመው የአካባቢው ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ እንዲሆኑ በማገዝ እንደሚደግፉ አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ የደሴ ከተማ አመራሮችና ባለሃብቶች ለሥራ ያላቸውን ተነሳሽነትም አድንቀዉ በኢንዶኔዥያ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ቃል ገብተዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር መለስ መኮንን በበኩላቸው የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች ከደሴ ባለህብቶች ጋር በማቆራኘት ልማትን ለማነቃቃት ለአምባሳደሩ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

“ለባለሃብቶች የወሎን ባህል፣ ታሪክና የመቻቻል እሴቶች በአለም ለማስተዋወቅም ምቹ ሁኔታን እንፈጥራለን “ብለዋል፡፡

በኢንዶኔዥያ ካሉ አቻ ከተሞች ጋርም የልምድ ልውውጥ በማድረግ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ደሴ በማምጣት ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር  ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አስታውቀዋል፡፡

“የከተማ አስተዳደሩ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ለኢንዱስትሪዎች ከኢንዶኔዥያ የሚያመጡትን አስፈላጊ ጥሬ እቃም በሚፈለገው ወቅትና ብዛት እንዲቀርብ ተነጋግረናል “ብለዋል፡፡

የሚልኩትን ምርቶችም የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸውም አስረድተዋል።

የአይጠየፍ አስመጭና ላኪ አክስዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ  አቶ አህመድ ሀሰን ኢንዶኔዥያ አምባሳደር በጋራ ለመስራት የተደረገላቸው ግብዣ ተቀብለው በመምጣታቸው አመሰግነዋል።

የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች ወደ ውጭ አገር ለመላክ ያሰቡትን ለማሳካት ከኢንዶኔዥያ ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውና ይህም ለስራቸው ቀና አንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ አህመድ “ከባለሃብቶቻቸው ጋርም በመወያየት ግንኙነታችንን በማጠናከር የልምድ ልውውጥ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ ነገ ደግሞ ከደሴ ከተማ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ጋር እንደሚወያዩና የአካባቢውን የመስህብ ስፍራዎችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም