ቀጥታ፡

ለዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲጠናከር ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 በውሃ ሀብት ዘርፍ ለተቀመጡ አገራዊ ግቦች ስኬትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ሊጠናከር ይገባል ተባለ። ትኩረቱን በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ ፍሳሽ አገልግሎትና ንጽህና ላይ አተኩሮ የሚሰራው የ'ዋን ዋሽ' አገር አቀፍ መርሃ ግብር ላይ ባለድርሻ ተቋማት በአዲስ አበባ እየመከሩ ነው። የምክክር መድረኩን የከፈቱት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ እንዳሉት ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የንጹህ ውሃ መጠጥ ተደራሽነትን 83 በመቶ ለማድረስ አቅዳለች። በንጹህና ጤናማ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ቁጥር አሁን ካለበት 17 በመቶ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2020 ወደ 70 በመቶ ለማድረስም ግብ ተቀምጧል። እስካሁን የዕቅዱን 68 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸው፤ በ2011ና 2012 በጀት ዓመት በመጠጥ ውሃ ዘርፍ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግና በስራዎች ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ሊደረስበት የታቀደውን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን አስታውሰዋል። ከንጹህ ውሃ መጠጥ፣ በጽዳት፣ በመጸዳጃ ቤት ግንባታ፣ የወንዞችና ውሃማ አካላትን መንከባከብ ስራዎች 'አንድ ዕቅድ፣ አንድ በጀትና አንድ ሪፖርት' በሚል በ'ዋን ዋሽ' መርሀ ግብር በመንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑና የልማት አጋሮች በቅንጅት እየተተገበረ ነው ብለዋል። የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ፣ የጤና ጥበቃ፣ የግብርናና የእንስሳት አብት ፣ የደን አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ፣ የትምህርት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት የሚፈጽሙት ፕሮግራም መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል። ከ'ዋን ዋሽ'ና ከውሃ ሀብት አስተዳድር መርሃ ግብሮች በተጨማሪ በድርቅ በሚጠቁ አካባቢዎች የሚከሰት የውሃ እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት 'ዘላቂ የውሃ አቅርቦት ፕሮግራም' የተሰኘ መርሃ ግብር በ2011 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበር መሆኑን ጠቁመዋል። ፕሮግራሙ ውሃን ከጉድጓድ በመቆፈርና ከወንዞች በመገደብ ረጃጅም ርቀት በቧንቧ ህዝብ በሰፈረባቸው አካባቢዎች በመውሰድ ለተጠቃሚው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት። አገሪቱ በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪና ግብርናው ዘርፍ ያቀደቻቸውን ግቦች ማሳካት የሚቻለው የውሃ ሀብትን በተቀናጀ አግባብ መምራት ሲቻል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም የባለድርሻ አካላት ትብብር ሊጠናከር ይገባል ብለዋል። የተቋማት ማስፈጸም አቅም፣ የገንዘብ እጥረት፣ በተደጋጋሚ የሚከሰት ድርቅና ጎርፍ፣ ፈጣን የህዝብ ቁጥር ዕድገት ከዘርፉ ችግሮች መካከል ዋናዎቹ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለመፍትሔው ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ውሃ በሁሉም ዘርፎች የሚገባ የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን አንስተው፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የፍሳሽና ንጽህ አገልግሎት ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር የዜጎች መሰረታዊ መብት በመሆኑ መንግስት የውሃን ሀብት በዘላቂነት ለመምራት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ተናግረዋል። በዎተር ኤድ የቴክኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ማናዬ ስዩም ከዚህ በፊት ሲተገበሩ በነበሩ ፕሮጀክቶች እያንዳንዱ አካል የራሱን ዕቅድ በተበታተነ ሁኔታ ይተገብር እንደነበር አስታውሰዋል። ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ባለው የ'ዋን ዋሽ' መርሃ ግብር ግን እንደ አንድ አገር በአንድ ዕቅድ በጋራ ለመስራት መሰረት ጥሏል ብለዋል። አሁንም የራሱ መሻሻል ያለባቸው ቅንጅታዊ አሰራሮች ቢኖሩም የተለያዩ ተቋማት በጋራ ለመስራት መፈራረማቸው በጋራ ለማቀድ፣ ተግባብቶ ለመተግበር፣ በጀትን በተቀናጀ ሁኔታ እንዲመራ ማድረጉን አብራርተዋል። በሌላ በኩል ከዚህ በፊት ከውሃ በቀር ለፍሳሽና ንጽህና ትኩረት እንደማይሰጥ አስታውሰው፤ በ'ዋን ዋሽ' ግን በትምህርት ቤቶች የውሃ፣ ፍሳሽና ንጽህና አገልግሎት ትኩረት ተሰጥቶት በጋራ እየተተገበረ መሆኑን በአወንታ አንስተዋል። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ወክለው የተናገሩት በዩኔሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ጊሊያን ሜልሶፕ የ'ዋን ዋሽ' ዓለም አቀፍ ፕሮግራም እስካሁን ከ2013 እስከ 2017 ዓመታት በንጹህ መጠጥ ውሃ 18 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል። በኢትዮጵያም በገጠር ነዋሪዎች፣ በትምህርትና ጤና ተቋማት ቅድሚያ በመስጠት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፤ ወደፊትም ዜጎች ንጹህ መጠጥ ውሃ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ መንግስት ለሚያደርገው ጥረት ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በተለይም በንጹህ መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ተደራሽነት የ2030 ዓለም አቀፋዊ የልማት ግቦች እንዲሳኩ የመንግስት ፕሮግራሞችን እንደሚደግፍ ነው የገለጹት። በዋን ዋሽ ፕሮግራም አንዱ ቁልፍ ጉዳይ በሆነው በንጽህና መስክ እስካሁን ከ200 በላይ ወረዳዎች የመጸዳጃ ቤት ግንባታና ተያያዥ ስራዎች ተተግብረዋል። ለውሃ ሀብትና ጤና ጉዳይ በአገሪቱ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ የሚነገርለት የፍሳሽና ንጽህና አገልግሎት ሽፋን ከ32 በመቶ እንደማይበልጥ መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም