መገናኛ ብዙሃን ሁሉንም አስተሳሰቦች እኩል በማስተናገድና የህዝብ አይንና ጆሮ ሆኖ የማገልገል ድክመት አለባቸው -የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

65
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2010 መገናኛ ብዙሃን ሁሉንም አስተሳሰቦች እኩል በማስተናገድና የህዝብ አይንና ጆሮ ሆኖ የማገልገል ድክመት እንዳለባቸው የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገልጿል። መገናኛ ብዙሃን ገለልተኛና ነፃ ሆነው እንዲሰሩ በማድረግ በኩል መንግስት ክፍተት እንዳለበት የሚዲያ ባለሙያዎች አመልክተዋል። “ሚዲያ ለፍትህና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፕሬስ ነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። የጽህፈት ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው እንደተናገሩት፤ ሚዲያው ሁሉንም አስተሳሰቦች እኩል በማስተናገድና የህዝብ አይንና ጆሮ ሆኖ እንዲያገለግል በማድረግ በኩል ድክመት ታይቶበታል። “የዘንድሮውን የፕሬስ ቀን ስናከብር የሚዲያው ዘርፍ ለፍትህና ዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ያለውን ድርሻ ተገንዝበን የፕሬስ ነፃነት በአገሪቱ እንዲከበር ጥረት ለማድረግ ቃል በመግባት ነው” ብለዋል። የኢትዮዽያ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ መሰረት አታላይ በኢትዮዽያ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ እንዲከበርና እንዲሻሻል በተደጋጋሚ ለመንግስት ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል። የህትመት ሚዲያው እንዲያድግ ከወረቀት አቅርቦትና ከህትመት አገልግሎት ድጋፍ ጀምሮ ሚዲያዎቹ ነፃ ሆነው እንዲሰሩ እስከመፍቀድ ድረስ መንግስት እገዛ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር የመጡትና የቀድሞው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ንጉስ ወዳጅነህ “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ነፃ ሆነው እየሰሩ አይደለም” ብለዋል። በተለይም የመንግስት ሚዲያ ተቋማት የተዋቀሩትና የሚመሩት በፖለቲካ ሰዎችና በሹመት በመሆኑ ጋዜጠኞች ከፍተኛ ጫና እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል። መንግስት የመገናኛ ብዙሃንን የፕሬስ ነፃነት አለማክበሩ የመንግስት ሚዲያዎች ተዓማኒነት እንዳይኖራቸውና ህብረተሰቡ ወደ ማህበራዊው ሚዲያ ፊቱን እንዲያዞር ማድረጉን ገልጸዋል። ከቁም ነገር መጽሄት የመጡት አቶ ታምራት ኃይሉ በበኩላቸው መንግስት ሚዲያዎቹን በበላይነት ከመቆጣጠር ይልቅ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በማድረግና የግል ሚዲያዎችን በማሳደግ አትራፊ መሆን ይችላል ብለዋል። የመንግስት ባለስልጣናት መረጃ ሲከለክሉ ጋዜጠኞች ወደ ፍርድ ቤት ሄደው መክሰስ እንደሚችሉ በህግ ከተቀመጠው ይልቅ ፈጣን እርምጃ ተወስዶ አስፈላጊው መረጃ በወቅቱ የሚገኝበት አሰራር እንዲፈጠርም ጠይቀዋል። በመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሚዲያ ልማትና ብዝሀነት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ታምራት ደጀኔ የፕሬስ ነፃነት እንዲተገበር ለማድረግ መንግስት የለውጥ መንገድ ውስጥ መግባቱን አብርተዋል፡፡ የፕሬስ ነፃነትን ማክበር ህገ መንግስቱን የማስከበር ጥያቄ በመሆኑ መንግስት ለሚዲያው ዘርፍ ልማትና ነፃነት ከግል ተቋማት ጋር በመሆን ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል። “የህትመት ሚዲያዎች ቁጥር እየተመናመነና ጋዜጠኞችም እየታሰሩ ነው” በሚል ለተነሳው ጥያቄ አሁን የታሰሩ የህትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ጋዜጠኞች እንደሌሉ አቶ ታምራት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም