ቀጥታ፡

ከአረንጓዴ አሻራ ቀን ጀርባ

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 24/2011 ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም አዲስ ነገርን አሳይታለች፡፡ በአንድ ጀምበር ይህን ያህል ችግኝ ከመትከል  ባለፈ የተተከሉ ችግኞች ቆጠራ የተከናወነበት ሂደትም እንደ አገር እንግዳ ነገርን አስተዋውቋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘኖች የተተከሉ ችግኞች ቁጥር በፍጥነት እየተቀበለ ይፋ የሚያደርግ ሶፍትዌር ገቢራዊ ያደረገ ሲሆን፤ ሂደቱንም የውጭ አገር ዴፕሎማቶችን ጨምሮ  በርካታ ሰዎች እንዲታዘቡት አድርጓል። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሶፍትዌሩን ለችግኝ ቆጠራ እንዲመች አድርገው ያበለጸጉት ከዚህ በፊት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ዲጅታላይዝድ በማድረግ ሂደት የተሳተፉ  ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መሆናቸውን አብራርተዋል። ቴክኖሎጂው በአደጉት አገራት በስፋት ለምርጫ እንደሚውል በመጠቆም። የቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ መዋል አንድ ወር ይፈጅ የነበረውን የችግኝ ቆጠራና ማጣራት ሂደት ወደ አንድ ቀን ዝቅ እንዲል ለማድረግ ማስቻሉን ገልጸዋል። ሂደቱ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ  ዘርፍ ተዓምር መስራት የሚችሉ ወጣቶችን ወልዳ ማሳደጓን ያሳየ መሆኑን ገልጸው፤ "ይህን አቅም አሰባስቦ ጥቅም ላይ ማዋል ደግሞ ከማህበረሰቡና ከመንግስት የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው" ብለዋል። የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው በመንግስት እቅድ እና ፕሮጀክት ህዝብን ማሳተፍ ከተቻለ የማይሳካ ነገር አለመኖሩን ጠቁመዋል። ከአረንጓዴ አሻራ ስኬት ጀርባ ያለው ምስጢር ህዝብ ጉዳዩን የራሱ እንዲያደርገው አስቀድሞ በመሰራቱ መሆኑን ተናግረዋል። "ሁነቱ እንደ አጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ለአገር ጥሪ አሁንም የማይሸራራፍ አቋም እንዳለቸው አስተምሮናል" ነው ያሉት። በአረንጓዴ አሻራ ቀን ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በተያዘ ዕቅድ መሰረት በዘመቻ የወጣው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከዕቅድ በላይ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች መትከሉ ይታወቃል። ይህም በዕለቱ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ሊመዘገብ ችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም