ቀጥታ፡

የአባይ ወንዝ የውሃ ፍሰት ሁኔታ የተሻለ መሆን በግድቡ ሙሌት ላይ ያለውን ውዝግብ ሊቀንሰው ይችላል ተባለ

ሐምሌ 24/2011 በቀጣይ አመት የሚኖረው በቂ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ  ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ውዝግብ ሊያረግብ እንደሚችል አለም አቀፍ የትንበያ አጥኚዎች ቡድን አመለከተ።

የህዳሴው ግድብ በሚገነባበት አካባቢ ከሰኔ እስከ ታህሳስ ባሉት ወራት የነበረው የእርጥበት ሁኔታ እንደሚቀጥል በአባይ ወንዝ ዙሪያ የአየር ንብረት ሁኔታን እየተከታተለ የሚያወጣው ብሉ ናይል ፎርካስት ግሩፕ (Blue Nile Forcast Group) የተሰኘ የትንበያ ቡድንን ዋቢ በማድረግ ኒው ሴኩሪቲ ቢት ድረ ገፅ አስነብቧል።

ከጆን ሆፕኪንስ፣ ከዊስኮንሲን ማዲሰን እና ከካሊፎርኒያ ሳንታ ባርባራ ዩኒቨርስቲዎች ከመጡ የጥናት ባለሙያዎች የተዋቀረው የትንበያ ቡድን ያወጣው መረጃ እንዳመለከተው እኤአ በ2018 በአካባቢው ከሰኔ እስከ ታህሳስ ይኖራል ተብሎ የተተነበየው 40 ሜትር ኪዩብ የውሃ ፍሰት የትንበያውን ትክክለኛነት አሳይቷል።

በ2019ኝም የላይኛው የአባይ ተፋሰስ ተመሳሳይ የሆነ የውሃ ፍሰትን ሊያስተናግድ እንደሚችል ቡድኑ ትንበያውን አስቀምጧል።

እንደ ቡድኑ ትንበያ በሁለቱ አመታት የታዩት የውሃ ፍሰት ሁኔታም እኤአ በ2020ም ሊቀጥል እንደሚችል ነው።

ከህዳሴው ግድብ ሙሌት ጋር በተያያዘ ግብፅ እየነሳችው ያለው የውሃ መጠን መቀነስ  ስጋት በዚህ ሊቀረፍ እንደሚችልና ውዝግቡ ለጊዜውም ቢሆን ሊረግብ እንደሚችል ቡድኑ በትንበያ ጥናቱ አብራርቷል።

ኢትዮጵያ እኤአ በ2022 የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዟን ያነሳው ድረ ገፁ እኤአ በ2020 የግድቡ ሙሌት የሚጀመርበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘም በአካባቢ የሚኖረው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ መቀጠሉ በግብፅ የሚነሳውን ቅሬታ ረገብ ሊያደርገው እንደሚችል የቡድኑን ትንበያ መሰረት በማድረግ ድረ ገፁ ዘግቧል።

ቡድኑ ትንበያውን ከማውጣቱ በፊት 16 አይነት ዘመናዊ የአየር ሁኔታ የጥናት ሞዴሎችን ተግባራዊ እንዳደረገና የትንበያ መዘርዝሮቹንም በሜይ 2018 እና 2019 ‘ክላይሜት ሃዛርድ ሴንተር’ በተሰኘ ብሎግ ላይ ማውጣቱን ኒው ሴኩሪቲ ቢት አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም