ኢትዮጵያ ከቻይናና ስሪላንካ ጋር የታዳሽ ኃይል ልማቷን ልታሰፋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከቻይናና ስሪላንካ ጋር የታዳሽ ኃይል ልማቷን ልታሰፋ ነው
ሐምሌ 24/2011 ኢትዮጵያ ከቻይናና ከስሪላንካ ጋር በመተባበር የታዳሽ ኃይል ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን ልታካሄድ ነው። ሦስቱ አገራት በደቡብ ለደቡብ ትስስር(South-South Cooperation) ያሏቸውን ልምድ በመለዋወጥ ፕሮጀክቱ በመጪው ሁለት ዓመታት ይካሄዳል ተብሏል። ቻይና በእነዚህ ዓመታት በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ለአንድ ፕሮጀክት አንድ ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግም ቃል ገብታለች። ቻይና ለስሪላንካ መንግሥትም በተመሳሳይ አንድ ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ ተጠቁሟል። ጎን ለጎንም ቻይና በመስኩ ያካበተችውን ልምድና ክህሎት ለኢትዮጵያና ለስሪላንካ መንግሥት እንደምታካፍልም ሥምምነት ላይ ተደርሷል። ድጋፉ የደቡብ ለደቡብ ትስስርን በማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና የንግድ አማካሪ ሊ ዩ ገልጸዋል። ድጋፉ የተደረገው በቻይና በቅርቡ በተካሄደው የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ስብሰባ ላይ ለታዳሽ ኃይል ትኩረት መሰጠቱን ተከትሎ መሆኑንም አንስተዋል። ድጋፉ በኢትዮጵያና በስሪላንካ ከታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማጎልበት ይረዳልም ብለዋል። በተለይም ደግሞ ሦስቱ አገራት ተቀራርበው እንዲሰሩ በማስቻል የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥም ያስችላል ነው ያሉት። የውኃ፣ የመስኖና የኢነርጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሀና በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የታዳሽ ኃይል አቅርቦቱን ለማስፋት እንደሚያግዝ ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ የባዮ ጋዝና የሶላር ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ድጋፉ ጠቃሚ መሆኑን በተወካያቸው በኩል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከ10 በመቶ በታች መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።