ቀጥታ፡

የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና አማራጮችን የሚያስተዋውቅ አውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

ሀምሌ 24/2011 በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና አማራጮችን የሚያስተዋውቅ አውደ ርዕይ የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው። አውደ ርዕዩን ያዘጋጀው 'ጎልደን ሚዲያና ኤቨንትስ' ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ነው። የጎልደን ሚዲያና ኤቨንትስ ስራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም አታክልት ከኢዜአ ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለምልልስ፤  የአውደ ርዕዩ ዓላማ መንግስት የሚያከናውናቸውን የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችና የማሻሻያ ስራዎችን ማስተዋወቅ ነው። በአሁኑ ወቅት እያደገ በመጣው የኢንቨስትመንት ዕድልና አማራጮቹ ዙሪያ በባለሀብቶች እና በትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የግንዛቤ እጥረት እንዳይኖር አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ማስተዋወቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል። በአውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት ዕድሎችና አማራጮች እንዲሁም በመንግስት እየተደረጉ ያሉ ማበረታቻዎችን አስመልክቶ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድም አቶ ቢንያም ጠቁመዋል። የፓናል ውይይቱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበርና  የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሚሳተፉበት ሲሆን እየተከናወኑ ባሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ዙሪያ የግሉ ዘርፍ  ሀሳቡን ያቀርባል ተብሎም ይጠበቃል። በአዲስ አበባ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጭና ዕድል የተደረገው የዳሰሳ ጥናት በአውደ ርዕዩ ላይ ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድበትም አቶ ቢንያም ገልጸዋል። ከፓናል ውይይቱና ከጥናታዊ ጽሁፉ ጎን ለጎን በግሉ ዘርፍ የሚገኙና በባንክ፣ በሪል ስቴት እና በአክሲዮን ሽያጭ ላይ የተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች ስራዎች ለተሳታፊዎች እንደሚደቀርቡም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድልና አማራጭ የማስተዋወቅ ስራ የመንግስት ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ቢንያም የግሉ ዘርፍም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል። በተለይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአገሩን የኢንቨስትመንት መስኮች በሚኖሩበት አገር በማስተዋወቅ አምባሳደር መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ጎልደን ሚዲያና ኤቨንትስ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና አማራጮችን ለማስተዋወቅ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመ ሲሆን በቀጣይም ከኮሚሽኑ ጋር መሰል ሁነቶችን በማዘጋጀት በውጭ አገር የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና አማራጮች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። አውድ ርዕዩን ከ500 አስከ 1 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም