ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትና ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ ለመወሰን የወጣው አዋጅ ጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትና ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ ለመወሰን የወጣው አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2011የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህዝብ ጥቅም ሲባለ የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትና ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን አዋጅ አጸደቀ። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ረቁቁን በአዋጅ ቁጥር 1161/2011 በአምስት ተቃውሞ፣ በአምስት ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። ከአዋጁ አንቀጾች መካከልም "ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ይግባኝ ማለት የሚፈልግ ከሆነ ልማቱ እንዳይጓተት ቦታውን አስረክቦ ክርክሩን የመቀጠል መብት አለው" የሚለው በአባላት ዘንድ ክርክር አስነስቷል። ቀድሞ የነበረው የካሳ ክፍያ አዋጅ ቁጥር 455/1997 ስራ ላይ ከዋለ ብዙ ዓመታት ያስቆጠረና ወቅታዊነት የጎደለው መሆኑ በውሳኔ ሃሳቡ ቀርቧል። በመሆኑም አሁን የጸደቀው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 የመሬት ባለይዞታዎችን ያሳተፈ፣ ጥቅማቸውን ያስከበረና በዘለቄታዊነት እንዲቋቋሙ የሚያስችል አሰራር የያዘ መሆኑም ተገልጿል። አዋጁ መሬት እንዲለቀቅ የሚወስነው አካል ሲወስን ለካሳና መልሶ ማቋቋም የሚያስፈልገው በጀትና በጀቱ በማን እንደሚወሰን በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑም ተገልጿል። በመላ ሀገሪቷ ወጥ የሆነ የካሳ አከፋፈልና ሂደቱን ተከትሎ ቅሬታ ማቅረብ የሚቻልበት የአሰራር ስርዓት የተከተለ መሆኑም ተገልጻል። ይሁን እንጂ በረቂቅ አዋጁ "ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ይግባኝ ማለት የሚፈልግ ከሆነ ልማቱ እንዳይጓተት ቦታውን አስረክቦ ክርክሩን የመቀጠል መብት አለው" የሚለው ሃሳብ ክርክር አስነስቷል። የምክር ቤት አባላት አንድ የልማት ተነሺ የተፈጥሮም ሆነ በህግ ሰውነት የተሰጠው አካል ንብረቱን ከተቀማ በኋላ ክርክር ማድረጉ ተገቢ አይደለም ብለዋል። ሂደቱ የተነሺዎችን የይግባኝ መብት የሚጥስ ብሎም ከፍትህ ሥርዓቱ ጋር የሚጋጭ መሆኑንም ጠቁመዋል። በመሆኑም "መሬቱን አስረክቦ ይግባኝ ማለት ይችላል" የሚለው ሃሳብ ወጥቶ ተነሽዎች የይግባኝ መብት ሊመቻችላቸው ይገባል በሚል ሃሳብ መቀየር አለበት ብለዋል። የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ ተነሽዎች ይግባኝ የሚሉት በንብረታቸው የካሳው መጠን እንጂ መሬቱን አልለቅም በማለት አይደለም ብሏል። የልማት ተነሺዎች በሚሰጣቸው የካሳ ክፍያ ካልተስማሙ ቅድሚያ ለይግባኝ ሰሚ ቅሬታ ማቅረብና እስከ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መሄድ ይችላሉ ነው የተባለው። ከዚህም በተጨማሪ ልማቱ እንዳይስተጓጎል የዜጎች መብትም እንዳይገደብ መሬቱ ስራ ላይ ውሎ የይግባኝ ክርክሩ መቀጠል እንደሚችል ተገልጿል። ይሁን እንጂ የልማት ተነሺዎች ይግባኝ የሚሉበት አቅም እንደሌላቸው በመረጃ ከተረጋገጠ መንግስት በነፃ የህግ አገልግሎት የሚሰጥበት እድል ይመቻቻልም ተብሏል።