የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት በንግዱ ውስጥ ሰርገው የገቡ የፖለቲካ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት በንግዱ ውስጥ ሰርገው የገቡ የፖለቲካ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት
ሐምሌ 24/2011 (ኢዜአ) የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት የአገሪቷን ሰላም ከማስጠበቅ በተጨማሪ በንግዱ ውስጥ ሰርገው የገቡ የፖለቲካ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታቁ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሰጡት አስተያየት፤ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱ እየተባበሰ የመጣው ሰላምና መረጋጋት ባለመኖሩ ና በንግዱ ውስጥ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ፖለቲከኞች ሰርገው በመግባታቸው ነው።
ለውጥ ከመምጣቱ በፊትም ጀምሮ የአገሪቱ ዋና ዋና የንግድ አውታሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካላት እጃቸውን አስገብተውበታል ሲሉም ተናግረዋል።
ለውጡን ተከትሎ ባለው ሂደትም በተለያዩ የሃገሪቷ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት ባለመኖሩ አርሶአደሩም ሆነ ሆነ የንግዱ ማህበረሰብ የተለመደ ስራውን ለማከናወን መቸገሩ አንድ ምክንያት ቢሆንም ከዚህ በተጨማሪ በአስመጭና ላኪ ስራ ላይ ያለው ሰንሰለት መፈተሽ አለበት ይላሉ።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ እንደሚሉት "ገበሬው መሸጥና መለወጥ አልቻለም፣ ሸማቹም ሸምቶ ኑሮውን ማሻሻል አልቻለም ወይም ደግሞ መነገድ አልቻለም።ይሄ ሰላም ስለታጣ ነው እህል ስለታጣ አይደለም ሰላም ስለሌለ ነው"።
አቶ ሀሪፉን ገብረእግዚአብሄ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር በበኩላቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች በፖለቲካ ሃይሎች ነው የተያዘው ሪፎርሙ እነዚህን ሁሉ ገና አላየም ይህም ሰው ሰራሽ እጥረት አምጥቷል" ብለዋል ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩትን ጨምሮ በርካታው ህዝብ ፖለቲከኛ መሆኑ በስራ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏልም ነው ያሉት።
በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎችም አባላቶቻቸውን ከማጥራት ጀምሮ ሁሉም የማህበረሰብ አካላት ሰላም እንዲረጋገጥ መስራት እንዳለበትና በተለይም ለይቅር ባይነትና ብሄራዊ መግባባት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
መንግስት በፖለቲካው ላይ እያመጣ ያለውን ለውጥ በንግዱ ዘርፍ ላይም ፍተሻ በማድረግ ሰው ሰራሽ እጥረት የሚፈጥሩ አካላትን ለይቶ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታልም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።