በመብራት መቆራረጥ ምክንያት በአቅማችን ልክ እየሰራን አይደለም...በገንዳ ውሃ ከተማ ባለሀብቶች - ኢዜአ አማርኛ
በመብራት መቆራረጥ ምክንያት በአቅማችን ልክ እየሰራን አይደለም...በገንዳ ውሃ ከተማ ባለሀብቶች
ሐምሌ 24/2011 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ በኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች በመብራት መቆራረጥ ምክንያት በአቅማቸው ልክ መስራት እንዳልቻሉ ቅሬታቸውን ተናገሩ፡፡ የክልሉ መስተዳድር በበኩሉ ባለሀብቶች ያሉባቸውን ችግሮች ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን እንደሚፈታ አስታውቋል፡፡ በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የተመራ የልኡክ ቡድን በዞኑ በኢንዱስትሪና በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችን የሥራ ሁኔታ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት በኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዳሉት በኢንዱስትሪ መንደሩ የግብዓት እጥረት ባይኖርም በመብራት መቆራረጥ ምክንያት በቀን ማምረት የሚገባቸውን ያክል እያመረቱ አይደለም። በኢንዱስትሪ መንደሩ በጥጥ መዳመጥ ሥራ የተሰማራው የ"ካልሚ ትሬዲንግ" ተወካይ አቶ ሰሎሞን ድረስ እንደተናገሩት ፋብሪካው በቀን ከ100 ኩንታል በላይ ጥጥ የመዳመጥ አቅም ቢኖረውም በኃይል መቆራረጥ ምክንያት እየሰራ ያለው በግማሽ ቀንሶ ነው፡፡ ከ60 በላይ ሰዎችን ቀጥሮ የማሰራት አቅም ቢኖርም በአሁኑ ወቅት ከ40 የማይበልጡ ሰራተኞችን ብቻ እየተጠቀመ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዚህም በሚፈለገው ልክ ማምረት ባለመቻሉ በገበያው ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት እንቃፋት እንደፈጠረበት ነው የገለጹት። የ"በልሰቲ ነገሳና ልጆቹ ትሬዲንግ" ገንዳ ውሃ ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ ክንዴ ደግነህ በበኩላቸው በ8 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሰሊጥ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ገንብተው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ፋብሪካው በቀን ከ500 ኩንታል በላይ ሰሊጥ በማበጠር ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም ቢኖረውም በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በቀን እያበጠረ ያለው 300 ኩንታል ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በእዚህም ፋብሪካው ለኪሰራ እየተጋለጠና ዘላቂ እድገቱም እየተገታ መሆኑን ጠቁመው ችግራቸው በፍጥነት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡ በአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የገንዳ ውሃ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነበረ የሱፍ በበኩላቸው የኃይል መቆራረጡ ችግር የተፈጠረው ለኢንዱስትሪ መንደሩ አገልግሎት የሚሰጠው ኃይል ለከተማው የነዋሪዎች ከሚቀርበው ኃይል ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡ በከተማው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ ጣቢያ መኖሩን የጠቀሱት አቶ ነበረ፣ "በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የኢንዱስትሪ መንደሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ለብቻው በቀጥታ እንዲያገኝ ይደረጋል" ብለዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው ወደ ማምረት የገቡ ባለሃብቶችን ችግር ለመፍታት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግ ገልጸዋል። በኢንዱስትሪ መንደሮች ያሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችንም ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመነጋገር ለመፍታት እንደሚሰራ ነው የገለጹት። ከመንግስት ቦታ ወስደው ሳያለሙ አጥረው የተቀመጡ ባለሃብቶች ካሉ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡም አሳስበዋል፡፡ በከተማዋ ባሉ የኢንዱስትሪ መንደር 42 ባለሀብቶች ወደ ሥራ ገብተው በማምረትና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ሲሆን አዲስ ውል የወሰዱና ሥራ ያልጀመሩ ዘጠኝ ባለሃብቶች እንደሚገኙ ታውቋል በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የተመራው የልኡካን ቡድን ትናንት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡ በኢንዱስትሪ መንደሩ የገቡ ባለሃብቶች ሰባት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን በግንባታ ላይ ባሉና ሥራ በጀመሩት ለ750 ቋሚና ከ1ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡