የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን - ወጣቶች
አዲስ አበባ ኢዜአ፤ ሃምሌ 24/2011 በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በበኩሉ ሠላም በማስፈንና በህግ የበላይነት መከበር ዙሪያ ከ25ሺ በላይ ወጣቶች ስልጠና መስጠቱን አስታውቋል፡፡
ብሔርን ከብሔር በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት ከሚሹ አካላት በመራቅ አሁን ለሰፈነው ሰላም መረጋገጥ የድርሻዋን እየተወጣች መሆኗን የተናገረችው የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት አያንቱ ጉደታ ናት።
ወጣት አያንቱ አንዳለችው የህግ የበላይነት እንዲከበር በማይሹ አክቲቪስቶችና ግለሰቦች የሚጻፉ ጽሁፎችን በማህበራዊ ሚዲያ ባለመከተልና የእነሱ ደጋፊ ባለመሆን ሠላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ሚናዋን እየተወጣች ነው።
መንግስት ወጣቱን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ተጨማሪ ስራዎች መስራት ይኖርበታል ያለችው ወጣት አያንቱ፤ ወጣቶች ጥያቄ ካላቸው በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ቀጣይነት ያለው ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ብላለች።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ታደሰ ጎሳዬ በበኩሉ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ግንባር ቀደም ተጋላጭ ወጣቱ እንደሆነ ገልጾ፤ አሁን ለመጣው ሀገራዊ ለውጥም መሪ ተዋናይ ሆኖ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የህብረተሰቡን ሠላም የሚያወኩ አካላትን ለህግ እንዲቀርቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ብርሃኑ ተካ በበኩሉ "ሰላም ከሌለ ዕድገት የለም፣ ብልጽግና የለም፤ እና ወጣቱ አንድ ሆኖ እጅ ለእጅ ተያይዞ ሰላሙን ማስጠበቅ አለበት " በማለት ይገልጻል።
"እኛ ወጣቶች በትናንሽ ጥቅሞች ተስበን የፖለቲከኞች መጠቀሚያ መሆን የለብንም"ያለው ወጣት ብሃኑ፤ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት ነገሮችን በሰከነ አዕምሮ መረዳት ያሥፈልጋል ይላል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና ጸሀፊ ወጣት ኤርሚያስ ማቴዎስ እንዳለው ፈዴሬሽኑ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከወጣቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።
ባለፉት ሁለት ወራትም ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡ ከ25ሺ በላይ ወጣቶች ሠላም በማስፈንና የህግ የበላይነትን በማስከበር ዙሪያ ስልጠና መስጠቱን ተናግሯል።
ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ የተሳሳቱ ሃሳቦች ስሜታዊ በመሆን ወደ ግጭት ሳይገቡ ከሚመለከተው አካል ጋር ሊወያዩ ይገባል ያለው ዋና ጸሐፊው፤ ወጣቶች ሁሉን ነገር መንግስት ብቻ እንዲያሟላ ከመጠበቅ ይልቅ የህግ የበላይነት እንዲከበር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ተናግሯል።
ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ከህጻናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባባር የወጣቱን ግንዛቤ የሚያሳድጉ የተለያዩ የሰላም ኮንፈረንሶችን እንደሚያዘጋጁም ነው የገለጸው።
በሌላ በኩል ከመጪው ነሐሴ ወር ጀምሮ ለሚካሄደው ከወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጎን ለጎን ወጣቶች የህግ የላይነትን በማስከበር ዙሪያ በክልሎች ያለውን ተሞክሮ እንዲለዋወጡ እንደሚደረግም ወጣት ኤርሚያስ ተናግሯል።
በሁሉም ክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳዳሮች የተጀመረው የሰላም አምባሳደርን የመለየት ተግባርም በቀጣይ ግዜያት እንደሚሰራ ነው የተገለጸው።