ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ብሔራዊ የህጻናትና ወጣቶች ስነምግባር ግንባታ ስትራቴጂ አዘጋጀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሐምሌ 24/2011- የፌደራል ስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ብሔራዊ የህጻናትና የወጣቶች ስነምግባር ግንባታ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን አስታወቀ። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ኮሚሽኑ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የህጻናትና ወጣቶች ስነምግባር ግንባታን አንድ የትኩረት መስክ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። “በነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ላይ በትኩረት ካልተሰራ ሀገሪቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ውስጥ ትወድቃለች” ያሉት አቶ ወዶ፤ የትውልዱ የስነምግባር ችግር ለሙስና እና ብልሹ አሰራር መባባስ በር እንደሚከፍትም ተናግረዋል። ለዚህም ከጉዳዩ አሳሳቢነትና አስፈላጊነት አኳያ ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቢሰራም የተፈለገው ውጤት እንዳልመጣ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ በህጻናትና ወጣቶች ስነምግባር ግንባታ ላይ እንደሚመሰረት አንስተው፤ ሀገርና ህዝብን ለመታደግ በትውለዱ ላይ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። በቀጣይም የስነምግባር ግንባታ ስትራቴጂን መንግስት እያዘጋጀው ካለው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጋር አስተሳስሮ ለመተግበር መታቀዱንም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የገለጹት። ለዚህም ኮሚሽኑ በአምስት ዓመት እቅዱ የህጻናትና ወጣቶች ስነምግባር ግንባታን በተቀናጀና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል ስትራቴጂ ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል። ስትራቴጂው ስለዛሬው ብቻ ሳይሆን ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ እጣ ፋንታ በማሰብ ህጻናት በመልካም ስነምግባር እንዲያድጉ የሚያስችሉ ተግባራትን እደያዘም ገልጸዋል። ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመጠየፍ ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለሀገሩ እድገትና ሰላም የሚያስብ ትውልድን መገንባት  የስትራቴጂው ትልቁ ግብ እንደሆነም አክለዋል። ለዚህ ሥራ ተግባራዊነት አግባብነት ያላቸው አካለት የተለዩ መሆኑና በስነምግባር ግንባታ ሂደቱ የሚጠበቅባቸው ተግባርና ተልዕኮም በዝርዝር መቀመጡን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት። በምሁራን የተቀረፀውና በሰፊ ውይይቶች ዳብሮ የተዘጋጀው ስትራቴጂ በ2012 ዓ.ም ወደ ተግባር እንደሚገባም አቶ ወዶ ገልጸዋል። በትግበራ ሂደቱም ቤተሰብ፣ መምህራን፣ ትምህርት ቤቶች እና የሃይማኖት ተቋማት የህጻናት ና ወጣቶች ስነምግባር ግንባታ ላይ እንዲሰሩ ሃላፊነት እንደተሰጣቸውም ተጠቅሷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም