ምክር ቤቱ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የአስተዳደር ምክር ቤት እና አካባቢያዊ ምርጫ እንዲራዘም ወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የአስተዳደር ምክር ቤት እና አካባቢያዊ ምርጫ እንዲራዘም ወሰነ
አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የአስተዳደር ምክር ቤት እና አካባቢያዊ ምርጫ እንዲራዘም ወሰነ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አራተኛ አመት የስራ ዘመን ሁለተኛው አስቸኳይ ስብስባ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የአስተዳደር ምክር ቤት እና አካባቢያዊ ምርጫዎች እንዲራዘሙ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የአስተዳደር ምክር ቤት እና አካባቢያዊ ምርጫዎች በተያዘው ዓመት መካሄድ የነበረባቸው ቢሆንም በውሳኔው መሰረት ምርጫዎቹ ተራዝመው በ2012 ዓ.ም ከሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ጋር የሚካሄዱ ይሆናል። ምክር ቤቱ የዛሬውን ውሳኔ ሊያስተላልፍ የቻለው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከቀረበለት ጥያቄ ተነስቶ ነው። ምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ለመመልመል፣ ለማሰልጠንና ለማዘጋጀት ጊዜ በመፈለጉና በዋነኛነት በክልል ደረጃ የተቋማት ለውጥ ስራ እየተካሄደ በመሆኑ የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የአስተዳደር ምክር ቤትና አካበቢያዊ ምርጫዎች እንዲራዘሙ ጥያቄ ያቀረበው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአሁኑ ሰአት ሁሉን አቀፍ የሆነ ለውጦችን እያካሄደ መሆኑን የገለጹት፤ የምክር ቤት አባል የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የአስተዳደር ምክር ቤትና አካበቢያዊ ምርጫዎች ከአገራዊ ምርጫው ጋር መካሄዳቸው ምርጫው ነጻ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል። በ2003 ዓ.ም በተመሳሳይ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የአስተዳደር ምክር ቤት እና አካባቢያዊ ምርጫዎች ተራዝመው እንደነበር የሚታወስ ነው።