ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ ቀን ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ከተነሡ፣ ያሰቡትን ሳያሳኩ እንደማይመለሱ ያረጋገጡበት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

ሐምሌ 23/2011 (ኢዜአ)   ''የአረንጓዴ አሻራ ቀን ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ከተነሡ፣ ያሰቡትን ሳያሳኩ እንደማይመለሱ ለሺኛ ጊዜ መልሰው ያረጋገጡበት ነው'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአረንጓዴ አሻራ ተሳታፊዎች የምስጋና መልክት አስተላልፈዋል። ዶክተር አብይ አህመድ ይህ አገራዊ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ከተነሡ፣ ያሰቡትን ሳያሳኩ እንደማይመለሱ ለሺኛ ጊዜ መልሰው ያረጋገጡበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ''የችግኝ እጥረት ባይገጥመንና ቀኑ ባይመሽ ኖሮ እንደ ሕዝቡ አወጣጥ ከዚህም በላይ የመሥራት ዐቅም ነበረን'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ''ከዚህ ሥራችን በበጎው እንደተደሰትን ሁሉ ከስሕተቶቻችንም እንማራለን'' ብለዋል፡፡ መውለድ ብቻ ልጅን እንደማያሳድገው ሁሉ መትከል ብቻ ዛፍን እንደማያጸድቀው በመገንዘብ የተተከሉትን ዛፎች መንከባከብ ተገቢ እንደሆነ አሳስበዋል። ሕዝቡ በተከላው ቀን ቃል በገባው መሠረት የእገሌ ሥራ ነው ሳይል የተከላቸውን ዞሮ ማየት፣ መንከባከብና ከጥቃት መከላከል እንዳለበት ገልጸዋል። የችግኝ ተከላው ከጫፍ አስከ ጫፍ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የማይረሳ ታሪካዊ አጋጣሚ እንደሆነ በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በችግኝ ተከላው ለተሳተፉት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ኢትዮጵያ 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል መርሃ ግብር ነድፋ ተግባራዊ በማድረግ እቅዷን ትናንት እውን አድርጋለች። በዚህም ኢትዮጵያ በህንድ አገር ተይዞ የነበረውን 66 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ቀን የመትከል የዓለም ሪከርድ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል ሪከርዱን በአምስት እጥፍ ማሻሻል ችላለች። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተላከው መግለጫ ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ከተነሡ፤ ካሰቡት ሳይደርሱ አይመለሱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ፡- • ስለማይበገረው ጽናታችሁ እና ሁሉን ማድረግ ስለሚችለው አስደናቂ አቅማችን በተለየ አክብሮት እና ፍቅር እጅ እነሳለሁ፡፡ • በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንኳን ሀገራችንን የሚመለከቱ አበይት ጉዳዮች ሲገጥሙን ከመቅጽበተ አይን ለሚያጋምደን- ያለምንም ልዩነት እንደ አንድ እናትና ልጅ ለሚያዛምደን እና ያለመለያየት ለሚያዋህደን ዘመን አይሽሬ ኢትዮጵያዊ መንፈሳችን ያለኝን የማይናወጥ ፍቅር በክብራችሁ ጥላ ስር ሆኜ በክብር እገልጻለሁ፡፡ • መቼም- ማንም የትኛውንም የክፋት ሴራ የሚሰራ የጥፋት አበጋዝ አብሮነታችንን ሊያጠለሽ ቢጥር እንኳን አብሮነታችን ከነፍሳችን ውስጥ የተሸመነ እንጂ ከስጋችን ላይ የተጎነጎነ አይደለምና አብሮነታችንን ላጸደቀው የአረንጓዴ አሻራ ድላችሁ የተለየ ምስጋናዬን በፍቅሬ ሙዳይ ሞሽሬ እነሆ ልኬያለሁ፡፡ ሀገር ታመሰግናለች- እኔም አመሰግናለሁ፡፡ የኢትዮጵያን አረንጓዴ ጸጋ በመመለስ አረንጓዴ አሻራ እንድናሳርፍ ያቀረብኩትን ጥሪ በመቀበል ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ለችግኝ ተከላ ወጥቷል፡፡ ከጨቅላ ሕጻናት እስከ ዘጠና ዓመት አዛውንት፣ ከጎዳና ተዳዳሪዎች እስከ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ፣ ከታክሲ ተራ አስከባሪዎች እስከ ጸጥታ አስከባሪዎች፣ ከገበሬዎች እስከ ግብርና ባለሞያዎች፣ ከልማት ጣቢያ ሠራተኞች እስከ ከፍተኛ ኤክስፐርቶች፣ ከተማሪዎች እስከ መንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከሀገር ቤት እስከ ዳያስፖራ፣ከድምጻውያን እስከ ተዋንያን፣ ከአትሌቶች እስከ እግር ኳስ ተጫዋቾች ተጨዋቾች፣ ከጋዜጠኞች እስከ ፊልም ባለሞያዎች፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ - ያልተሳተፈ የኅብረተሰብ ክፍል አልነበረም፡፡ ይህ የተሳትፎ ማእበል እና የእምቢ ለሀገሬ ሆታም በታሪክ ማህደር ላይ መቼም አይረሳም፡፡ ሕዝቡ አረንጓዴ አሻራውን ለማኖር የነበረውን ትጋትና ቆራጥነት የሚያሳዩ አስደናቂ ክንዋኔዎችን አይተናል፡፡ የአረንጓዴው አሻራ አርበኛ ከማለዳው 12 ሰዓት አስቀድሞ ወጥቷል፡፡ አያሌ ባለሀብቶች መኪኖቻቸውን በራስ ተነሣሽነት አንቀሳቅሰዋል፤ ዳያስፖራዎች በገንዘባቸው አግዘዋል፤ ኮርፖሬሽኖች ኃላፊዎቻቸውንና ሠራተኞቻቸውን አሠማርተዋል፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞች ራሳቸውን አደራጅተው አሻራቸውን ለማኖር ወጥተዋል፤ ሙሽሮች በሠርጋቸው ዕለት ሱፍ- ቬሏቸውን ልብሰው ተገኝተዋል፤ ችግኝ ተካዮችን ለማበረታታት ቀረርቶ፣ ሽለላ፣ ፉከራ፣ ባሕላዊ ዘፈን እና እልፍ አእላፍ የህብር ሆታ በመላ ኢትዮጵያ- በመላ ኢትዮጵያውያን ቋንቋ እና ባህል ከጫፍ እስከ ጫፍ ተስተጋብቷል፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የሃይማኖት አባቶች ተከላውን በጸሎት አስጀምረዋል፤ እናቶች ምግብና መጠጥ አዘጋጅተው ለተካዮች አቅርበዋል፤ ወደ ውጭ የሚጓዙ ሰዎች የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት በዋዜማው ተክለዋል፤ ሚዲያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ዜናውን ለመሸፈን ተቀናጅተው ሠርተዋል፤ ዓይነ ሥውራን በኬን፣ አካል ጉዳተኞች በዊል ቸር፣ ወላጆች አራስ ልጆቻቸውን አዝለው ለተከላው ተሠማርተዋል፡፡ ልጆች በእናታቸው እቅፍ፣ አረጋውያን በከዘራ ወደ ተራሮች ተምመዋል፡፡ ችግኝ ባጠረባቸው ቦታዎች ዜጎች በገዛ ገንዘባቸው እየገዙ ሀገራዊ ተልዕኳቸውን ተወጥተዋል፡፡ ሀምሌ 22 ማለዳ ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር የነገሰው ትጋት፣ አብሮነት፣ ፍቅር፣ ተነሳሽነት፣ ጽናት እና የእናሳካዋለን ስሜት ችግኝ ከመትከልም በላይ የሚገለጽ ድንቅ ድል አጎናጽፎን በድል ተጠናቋል፡፡ የሐምሌ 22ቱ ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ሕዝቡ በአንድነት ወጥቶ ችግኝ የተከለበት ብቻ ሳይሆን ሐሳቡን የገለጸበትም አጋጣሚ ነበር፡፡ ሀገሩን የሚወድ፣ ለሀገሩ የሚጠበቅትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ የሆነ፣ ለትክክለኛ ዓላማ የሚያሠማራው ሲያገኝም አንድ ሆኖ የሚነሣ ሕዝብ እንዳለን አይተናል፡፡ ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት፣ ከግላዊነት ይልቅ ሕዝባዊነት፣ ከራሱ ይልቅ ለሀገሩ፣ ከሆዱ ይልቅ ለክብሩ የሚሞት ሕዝብ እንዳለንም ነግሮናል፡፡ ከትናንሽ አጀንዳዎች ይልቅ ታላላቅ ሀገራዊ ግዳጆች የሚማርኩት ሕዝብ መሆኑን ገልጾልናል፡፡ ከአቧራ ይልቅ ለአሻራ ቦታ የሚሰጥ ሕዝብ መሆኑን በማያወላዳ መልኩ አስረግጦ አስረድቶናል፡፡ ታላቅ ሐሳብ የሚማርከው ታላቅ ሕዝብ መኖሩን አመላክቶናል፡፡ ችግር ነቅሎ ችግኝ የሚተክል ሕዝብ እንዳለንም በውል ተረድተናል፡ ይህ ታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮ እንዲሳካ የበኩሉን ያልተወጣ የኅብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ ነገር ግን ከጣት ጣት ይበልጣል እንደሚባለው የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ወገኖች አሉ፡፡ ሂደቱን የመራው ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት፣ ሂደቱን ያስፈጸሙት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት፣ መረጃው የተሰባሰበበትን መንገድና ሶፍት ዌር ያዘጋጁ ባለሞያዎች፣ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች፣ እስከ ችግኝ መትከያ ጣቢያ ድረስ በተዘረጋው መረብ ተሠማርተው መረጃውን እያጣሩ ሲያሰባስቡ የነበሩ የመረጃ ወኪሎች፣ የተስተካከለ መረጃ ብቻ እንዲመዘገብ ሲከታተሉ የነበሩ የመረጃ አጣሪዎች፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቀናጅተው ሲሠሩ የነበሩ መላው የሀገራችን ሚዲያዎች፣ ለኅብረተሰቡ ትምህርት ሲሰጡና ሲያቀናጁ የነበሩ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች፣ የየመሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች፤ ላከናወናችሁት የላቀ የመሪነት ተግባር በራሴና በኢፌዴሪ መንግሥት ስም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህ ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ከተነሡ፣ ያሰቡትን ሳያሳኩ እንደማይመለሱ ለሺኛ ጊዜ መልሰው ያረጋገጡበት ነው፡፡ 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዐቅደን ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተክለናል፡፡ የችግኝ እጥረት ባይገጥመንና ቀኑ ባይመሽ ኖሮ እንደ ሕዝቡ አወጣጥ ከዚህም በላይ የመሥራት ዐቅም ነበረን፡፡ ከዚህ ሥራችን በበጎው እንደተደሰትን ሁሉ ከስሕተቶቻችንም እንማራለን፡፡ ይህ ተግባር የአንድ ቀን ዘመቻ ብቻ አይደለም፤ ክረምቱን ሙሉ የምንሠራው ነው፡፡ ሀገራችን እንደ ስሟ ለምለም እስክትሆን ድረስ በየዓመቱ እንቀጥልበታለን፡፡ ያገኘናቸውን በጎ ነገሮች አጠንክረን፣ ድክመቶቻችንን አርመን ቀጣዩን የተሻለ እናደርገዋለን፡፡ ከሀገራችን ጥቁር ሰማይ ስር በጥቁር መዳፍ የተሸመነ አረንጓዴ ሸማ ጥቁር አፈራችን ላይ እንዘረጋለን፡፡ የታላቅነታችን ሚስጥር የተሰቀለችበትን ክር ጠንቅቀን የምናውቅ ህዝቦች ነንና ከአዝማናት ታላቅነታችን ጋር እንደገና እንገናኛለን፡፡ መውለድ ብቻ ልጅን እንደማያሳድገው ሁሉ መትከል ብቻ ዛፍን አያጸድቀውም፡፡ የወለድናቸውን ማሳደግ፣ የተከልናቸውንም መንከባከብ አለብን፡፡ ሕዝቡ በተከላው ቀን ቃል በገባው መሠረት የእገሌ ሥራ ነው ሳይል የተከላቸውን ዞሮ ማየት፣ መንከባከብና ከጥቃት መከላከል አለበት፡፡ ባለ ሀብቶች ባለሞያ መድበው የተከሏቸውን ችግኞች እንደሚያሳድጉ አምናለሁ፤ ወጣቶች የተከሏቸውን ችግኞች ለማየት ወደ ተራሮች ስፖርት እየሠሩ እንደሚወጡ ተስፋ አደርጋለሁ፤ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞችም ተራ ገብተው ችግኞቻቸው የት እንደደረሱ እንደሚጠይቁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የተከልናቸውን ችግኞች የማሳደግ ሀገራዊ ዐቅማችን ከ50 በመቶ በታች ነው፡፡ ይህን ውሱንነት በመቅረፍ ቢያንስ በቀጣዮቹ ዓመታት ወደ 70 በመቶ ማሳደግ አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ወልዶ ማሳደግ የሚያውቅበት የሀገሬ ሕዝብ ተክሎ በመንከባከብ ታሪክ እንደሚሠራ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ለአረንጓዴ አሻራ ቀን ስኬት የሚጠበቅባችሁን ሁሉ ያደረጋችሁ ሁሉ ታሪክን በደማቅ ቀለም ጽፋችኋልና በድጋሚ አመሰግናችኋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ ሠሪ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!   ሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም