ቀጥታ፡

መንግስት የአልጀርስ ስምምነትን ከመተግበሩ በፊት ህዝቡን ያወያይ- መኢአድ

አዲስ አበባ 5/2010 መንግስት የአልጀርስ ስምምነትን ተቀብሎ ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት ህዝቡን እንዲያወያይ መኢአድ ጠየቀ። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የአልጀርስ ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔን ለመፈፀም ገዢው ፓርቲ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ፓርቲው እንዳለው ጉዳዩ በገዢው ፓርቲ ብቻ የሚወሰን አይደለም። መንግስት ስምምነቱን ተቀብሎ ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት የኢትዮጵያን ህዝብ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና በድንበር አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን ማወያየት ይኖርበታል ነው ያለው። ፓርቲው 'የአልጀርስ ስምምነት ይዘት የአገርና የህዝብን ጥቅም የሚጎዳ በመሆኑ ውሳኔው እንደገና ማጤን ይኖርበታል' ሲልም አሳስቧል። የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ የአካባቢው ማህበረሰቦች ማንነት ላይ አደጋ የሚጥልና ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ መኢአድ ይቃወመዋል ብሏል። ፓርቲው ውሳኔውን በመቃወም የተደረጉትን ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚደግፍም አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከኤርትራ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ለመፈፀም መወሰኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም