ቀጥታ፡

የዳሽን ባንክ ሰራተኞች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ

ሀምሌ 23/2011 የዳሽን ባንክ አክሲዮን ማህበር ሰራተኞች በዛሬው ዕለት በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ “ጣሊያን ምሽግ” በሚባለው አካባቢ ከአንድ ሺህ በላይ ችግኝ ተክለዋል። ሰራተኞቹ የተከሉትን ችግኝ በዘላቂነት የመንከባከብ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል። የዳሽን ባንክ የአርበኞች ቅርንጫፍ ስራ እስኪያጅ አቶ ወንድምአገኝ ጌታቸው እንደገለጹት ፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ችግ ባንኮችንም የሚነካ በመሆኑ በዘርፉ የተሰማራ ሁሉ ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት። በተጀመረው አገረዊ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት የተገኘው ስኬት አገሪቱን በአለም እንድትታወቅ ማስቻሉን አንስተዋል። ወደፊት አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ የሚሆን በመሆኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተተከሉ ችግኞችን በፕሮግራም እንደሚንከባከቡ አቶ ወንድምአገኝ የገለጹት። የአካባቢውን የደን ልማት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የሚንከባከቡት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር ስራ እስኪያጅ ወይዘሮ መሶብወርቅ ቅጣው በበኩላቸው አዲስ አበባን አረንጓዴ በማድረግ ለቱሪስት ምቹ እንድትሆን መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። በዘንድሮው የክረምት ወቅት አራት ቢሊዮን ዛፍ ለመትከል በተያዘው ዕቅድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እየተሳተፈ ነው። በመሆኑም ዕቅዱን ለማሳካት የሚቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ይገኛል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም