ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ዘመቻ የተመድና የአፍሪካ ህብረት ቀዳሚ አጀንዳ ነው - አምባሳደር አዲኦዬ

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 23/2019 የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ዘመቻ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና የአፍሪካ ህብረት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን በኢትዮጵያ የናይጄሪያ አምባሳደር ገለጹ። በዘንድሮው የክረምት ወቅት አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የሚያስችል የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት ይፋ መደረጉ ይታወቃል። በኢትዮጵያ የናይጄሪያ አምባሳደርና የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የናይጄሪያ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ባንኮሌ አዲኦዬ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ዘመቻ ለናይጄሪያ፣ ለቀጣናው አገራትና ለመላው አፍሪካ አዎንታዊ መልዕክት አለው። የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብሩ የተመድ ዘላቂ ልማትና የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ዋና አካል እንደሆነም ጠቁመዋል አምባሳደሩ። የአፍሪካ ህብረት በአጀንዳ 2063 ካስቀመጣቸው ዋና ዋና ግቦች መካከል ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን የሚያረጋግጥና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት አንዱ እንደሆነም ገልጸዋል። አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጡን በማስከተሉ ያላት ድርሻ ዝቅተኛ ቢሆንም አህጉሪቷ ለውጡ በሚያደርሰው ችግር ግን ቀዳሚ ሰለባ እንደሆነችም ተናግረዋል። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ እንደ ድርቅ፣ ጎርፍና ከፍተኛ ሙቀት ያሉ አደጋዎች የአህጉሩቱን ሁለንተናዊ ገጽታ እየጎዳ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በዚህ የክረምት ወቅት የያዘችው የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር የፓሪስ ስምምነት የሆነውን የተመድ አየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍንም በአህጉሪቱ ለመፈጸም መንገድ የሚከፍት ጅምር እንደሆነ አብራርተዋል። በተለይም በምዕራብ አፍሪካ ቀጣና በረሃማነትን ለመከላከል የተነደፈውን 'ታላቅ የአረንጓዴ ግንብ' ስትራቴጂ እውን ለማድረግ ከኢትዮጵያ ትምህርት መውሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል። ''እጅግ በርካታ ችግኝ በመትከል ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን ማረጋገጥ እምነት አለኝ'' ያሉት አምባሳደር አዲኦዬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ቀን የናይጄሪያ ኤምባሲ ተጋብዞ የታሪኩ ተጋሪ ለመሆን በመቻሉም ምስጋናቸውን አቅርዋል። ትናንት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 23 ሚሊዮን የሚገመት የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፏል። በመርሐ ግብሩ ከ353 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተተክሏል። የችግኝ ተከላው ከልጅ እስከ አዋቂ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችና በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጭምር ተሳትፈውበታል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም