የአሰልጣኝ ከማል አህመድ የታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክት በወራቤ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የአሰልጣኝ ከማል አህመድ የታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክት በወራቤ ተከፈተ
ሀምሌ 23/2011በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የአሰልጣኝ ከማል አህመድ የታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክት ተከፈተ።
ፕሮጀክቱ ከትናንት በስቲያ በወራቤ ስታዲየም ሲከፈት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሳዳት ጀማል ተገኝቷል። የታዳጊ እግር ኳስ ፕሮጀክቱ ዓላማ የስልጤ ወራቤ እግር ኳስ ክለብን ማጠናከር ሳይሆን ለሁሉም ክለቦችና ለብሔራዊ ቡድን ብቁና ተተኪ ተጫዋቾችን ማፍራት እንደሆነ አሰልጣኝ ሳዳት ጀማል ለኢዜአ ገልጿል። ዕድሜያቸው ከ8-17 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች በሣምንት ለስድስት ቀናት ስልጠና የሚወስዱ ሲሆን ፕሮጀክቱ እስከ 250 የሚደርሱ ታዳጊዎችን እንደሚቀበል አስታውቋል። የታዳጊዎች ምዝገባ ከሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ትናንትናና ዛሬ ከመቶ በላይ ታዳጊዎች ተመዝግበዋል። ምዝገባው እስከ ሐምሌ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። የተመዘገቡት ታዳጊዎችም ከሐምሌ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአሰልጣኝ ሳዳት ጀማልና አሰልጣኝ ከማል አህመድ እንዲሁም ከስልጤ ዞን በተገኙ ሦስት የታዳጊ ፕሮጀክት አሰልጣኞች ስልጠና ይጀምራሉ። ስልጠናው የተሻለ የእግር ኳስ ክህሎት ያላቸውና የሌላቸው በሚል ሁለት ምድብ ተከፍሎ እንደሚሰጥ አሰልጣኝ ሳዳት ገልጿል። የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ባለሀብቶች እስካሁን ለፕሮጀክቱ ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የስፖርት ትጥቆችና ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል። በቀጣይም አሰልጣኝ ከማል አህመድና አሰልጣኝ ሳዳት ጀማል በስልጤ ዞን ከ2012-2016 ዓ.ም በስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ የከማል የታዳጊዎች የእግር ኳስ አካዳሚን ለመገንባት ዕቅድ እንዳላቸውም ጠቁሟል። አካዳሚውን ለመገንባት የሚያስችል ፈቃድ ከክልሉ ማግኘቱን የገለጸው አሰልጣኝ ሳዳት ግንባታውን ማከናወን የሚያስችል ትልመ ሀሳብ /ፕሮፖዛል/ ለዞኑ አስተዳደር ማቅረቡን አመልክቷል። ለአካዳሚው ግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ ከደቡብ ክልል መንግስት፣ ከስልጤ ዞን አስተዳደር፣ ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን፣ ከወራቤ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ከባለሀብቶች ለመሰበስብ መታቀዱንም አክሏል። የታዳጊዎች የእግር ኳስ አካዳሚን በተመለከተ አሰልጣኝ ሳዳትና አሰልጣኝ ከማል ኳታር ሄደው ልምድ እንዲቀስሙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቃል መግባቱን ተናግሯል። በመልካም ስነ ምግባር የታነጹና ለብሔራዊ ቡድን የሚመጥኑ ብቁ ተጫዋቾችን ማፍራት እንዲሁም ታዳጊ ወጣቶች አልባሌ ቦታ ውለው ለሱስ እንዳይጋለጡ ማድረግ የአካዳሚው ዓላማ እንደሆነም ገልጿል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በፕሮጀክቱ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ እንዳሉት፤ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የተጫዋቾች እጥረት ለማቃለል የታዳጊዎች የእግር ኳስ አካዳሚ ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት ወሳኝ ነው። የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ አቶ ሞገስ ወምበሬ በበኩላቸው የከማል የታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክት መከፈት የህብረተሰቡን ተሳትፎ ከማረጋገጥ በላይ ታዳጊዎች የተሟላ ስብዕና እንዲኖራቸውና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል፡፡ በክልሉ ከሚገኙ 76 የታዳጊ ፕሮጀክቶች የስልጠና ማዕከላት መካከል 46ቱ በእግር ኳስ ላይ እንደሚሰሩ ተጠቁሟል። በ2008 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ስራ የጀመረው የከማል የታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክት በሁለቱም ጾታዎች በአጠቃላይ 180 ታዳጊዎችን ተቀብሎ እያሰለጠነ እንደሚገኝ ተገልጿል።