በብራዚል እስር ቤት በተነሳ ሁከት 57 ሰዎች ሞቱ

63

ሐምሌ 23/2011 በሰሜናዊ ብራዚል አልታሚራ እስር ቤት በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት 57 ሰዎች መሞታቸውን የእስር ቤቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ከሟቾቹ መካከል 16 የሚሆኑት በዘግናኝ ሁኔታ ህይወታቸው ሲያልፍ ቀሪዎቹ የእስር ቤቱ ህንፃ ሲቃጠል በተፈጠረ መታፈን ጉዳት እንደደረሰባውቸው የፓራ ግዛት የእስር ቤቶች አስተዳደር መናገራቸውን  አልጀዚራ በዘገባው አመልክቷል።

ሁሉን አካባቢ ያማከለ አሰሳ ሲደረግ የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የግዛቱ የእስር ቤቶች አስተዳደር ሀላፊ  ጃርባስ ቫስኮንስሎስ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል።

በአልታሚራ እስር ቤት በወንጀል ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ግጭት ማለዳ ላይ ቁርስ በሚቀርብበት ጊዜ እንደተጀመረ ቫስኮንስሎስ መናገራቸውን ዘገባው አስፍሯል ፡፡

አንደኛው የእስረኞች ቡድን የሌላኛውን የእስረኞች ክፍል ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራ እንደሆነ በዘገባው የተገለፀ ሲሆን የጥቃቱን መንስኤ ለማወቅ ምርመራ እንደሚደረግም የብራዚል ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ብራዚል ከዓለም ሦስተኛዋ ከፍተኛ የእስረኞች ቁጥር ያለባት ሀገር እንደሆንች  እ.ኤ.አ. በሰኔ 2016 ይፋ የተደረገው አኃዛዊ መረጃ ማመላከቱንም ዘገባው አስፍሯል።

የታራሚዎች ቁጥር ከእስር ቤቶች አቅም በእጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በተጠቀሰው አመት 368ሺ 049 ሰዎች እስር ላይ እንደሚገኙ ይገመታል።

በብራዚል እስር ቤቶች ባለው ከፍተኛ መጨናነቅ በቡድን አመፅ፤ ሁከት መፍጠር እና የማምለጥ ሙከራ ማድረግ የተለመደ እንደሆነ አልጀዝራ በዘገባው አስታውሷል።

 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም