የደን ልማት የአደጋ ስጋት መከላከል አካል በመሆኑ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል-አቶ ምትኩ ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
የደን ልማት የአደጋ ስጋት መከላከል አካል በመሆኑ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል-አቶ ምትኩ ካሳ
አዲስ አበባ ሀምሌ 23/2011 የደን ልማት የአደጋ ስጋት መከላከል አካል በመሆኑ በዘመቻ ሳይሆን በመደበኛ ተግባር በቀጣይነት መስራት ይገባል ሲሉ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ተናገሩ። ኮሚሽነሩ የደን ልማት ስራው ውጤታማ እንዲሆን ህብረተሰቡን ከደን ጋር የሚያስተሳስሩ የግብርና ስራዎችን አብሮ መስራት ይገባልም ብለዋል። ከሰላም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰራተኞች ትናንት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ በመሄድ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል። በስፍራው ከሰራተኞች ጋር ችግኝ ሲተከሉ ያገኘናቸው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የደን ልማት ስራ ተቋማቸው ከሚሰራቸው የአደጋ ስጋት መከላከል ስራዎች አካል አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ይገልጻሉ። የጎርፍና የድርቅ አደጋዎች መከሰት ዋነኛው መንስኤ ከደን ሃብት መመናመን ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸው፤ ችግኝ ተከላው በዘመቻ ሳይሆን በመደበኛ ስራ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ቢሰራበት የአደጋ ስጋትን መቀነስ ያስችላልም ብለዋል። ቸግኞች ከተተከሉ በኋላ የጽድቀት መጠናቸው ውጤታማ እንዲሆን ደን ከማህበረሰቡ ጋር የሚተሳሰርበትን አጋጣሚ መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ደኖች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቡና፣ በማርና በቅመማ ቅመም ምርቶች የተሳሰሩ በመሆናቸው ማህበረሰቡ በባለቤትነት ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ለአብነት አንስተዋል አቶ ምትኩ። በዚህም በሌሎች አካባቢዎችም የሚለሙ የማህበረሰብ ደኖች ከሰው ህይወት ጋር እንዲቆራኙ እንደየአካባቢው አየር ንብረት ለማህበረሰቡ ጥቅም የሚሰጡ ፍራፍሬዎችም ሆኑ ሌሎች ከግብርና ምርታማነት ጋር የተያያዙ ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሚገኙ ሃይቆች ጥልቀት እየቀነሱና ግድቦች በደለል እየተሞሉ በመሆናቸውም የከፋ አደጋ ስጋት እንዳለ የሚገልጹት ኮሚሽነሩ፤ ልዩ ትኩረት የሚገባቸው ተፋሰሶችን በደን መሸፈን ተገቢ ነው ይላሉ። የህዳሴ ግድብን እንደ አብነት አንስተው ወደፊት ግድቡ አሁን ላይ በሌሎች ግድቦችና ሃይቆች ላይ የሚስተዋለው የደለል መሞላት አደጋ እንዳይገጥመው የአባይ ወንዝና ገባሮችን ያማከለ የአፈር መከላከል የቤት ስራዎችን መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል። ስለሆነም አገራዊ የደን ልማት መርሃ ግብር ቢኖርም ልዩ ትኩረት የሚሹ አካባቢዎችን ለይቶ የሃይቆችን ዙሪያ ከእርሻ ነጻ የማድረግና የወንዝ ዙሪያ ገባን በደን መሸፈን እንደሚገባም ነው ያብራሩት።