ቀጥታ፡

11 አገሮችን በማሳተፍ በአሜሪካና በኢትዮጵያ ትብብር የተሰጠው ወታደራዊ ስልጠና በቀጠናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ያግዛል

ሀምሌ 23/2011 አስራአንድ አገሮችን በማሳተፍ በአሜሪካና በኢትዮጵያ ትብብር የተሰጠው ወታደራዊ ስልጠናው በቀጠናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አሜሪካ ገለጸች። በአሜሪካ መንግስት አሰልጣኝነትና በኢትዮጵያ ጋባዥነት ለ15 ቀናት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል። በስልጠና ማጠናቀቂያ መርሃ ግብሩ ላይ በአፍሪካና ደቡባዊ አውሮፓ የአሜሪካ ጦር ግብረ ሃይል ምክትል አዛዥ ሌተናል ጄነራል ላፕቲ ፍሎራ እንደገለጹት፤ የተሰጠው ወታደራዊ ስልጠና በቀጠናው ያለውን የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል። በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እየተስፋፋ የመጣውን የአሸባሪነት ተግባር የመግታት የሚያስችል አቅም የመገንባት ዓላማ ይዞ በተካሄደው ስልጠና ኢትዮጵያ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጂቡቲ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድ፣ ሶማሊያና ኡጋንዳ ተሳትፈዋል። በስልጠናው በሚሳተፉ ወታደሮች ብዛት ኢትዮጵያና አሜሪካ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን ባጠቃላይ ከ1 ሺህ 100 በላይ ወታደሮች ተሳትፈዋል። ሌተናል ጄነራል ላፕቲ እንዳሉት፤ ስልጠናው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ጦርን (አሚሶም) ከማጠናከር ባለፈ አገሮቹ በቀጠናው ላይ በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያስችል ነው። የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ሃላፊ ተወካይ ብርጋዴር ጄነራል ሃብታሙ ጥላሁን በበኩላቸው ሰልኞቹ አሸባሪነትን ለመዋጋት የሚያስችላቸውን እውቀትና ክህሎት እርስ በርስ በመማማር የቀሰሙበትና ውጤት ያመጣ እንደሆነ ገልጸዋል። ''የስልጠናው ተሳታፊ አገሮች በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን የማምጣት ግብን እንጋራለን'' ያሉት ጄነራሉ ስልጠናው በሶማሊያ ስጋት የሆነውን አልሸባብን ለመግታት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። የሽብር ጥቃት ውስብስብ ከመሆኑ አንፃር በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑንና ኢትዮጵያ በተለያዩ አለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ስር በመሳተፍ የጎላ ሚና እያመጣች መሆኑንም ጠቅሰዋል። ለዚህም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦባማ ስለ ኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በቀጠናው ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን መመስከራቸውን አስታውሰዋል። ከስልጠናውን የተገኘውን ክህሎት በተግባር ላይ በማዋል በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በተለይም በሶማሊያ የአሸባሪነትን ተግባር ለመግታት መስራት እንደሚገባም ብርጋዴር ጄነራል ሃብታሙ አስገንዝበዋል። የስልጠናው የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ በአሜሪካ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን በውትድርና ውስጥ የሚካሄዱ የማጥቃትና የመከላከል፣ የህክምና አሰጣጥ፣ የጋዜጠኞች የዜና አዘጋገብ፣ ወታደራዊ ቁሳቁሶች (ሎጂስቲክስ) አቀራረብና ሌሎች ዘርፎችንም ያካተተ ስልጠና መካሄዱን ለማወቅ ተችሏል። በቀጠናው የሚታዩ የአሸባሪነት እንቅስቃሴዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሁሉም አገሮች ስጋት ነው። በተለይም በቀጠናው እየተበራከቱ የመጡት የሽብርተኝነት ድርጊቶች፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና መሰል ድርጊቶች የቀጠናውን አገሮች ጨምሮ የሌሎች አለም አቀፍ አገሮች ስጋት እየሆነ መጥቷል። ስልጠናው በቀጠናው ያለውን የሰላም ማስከበር ስራ ከማጠናከር ባሻገር አገሮቹ በራሳቸው ያላቸውን ወታደራዊ አቅም እንዲያጠናክሩ የሚያስችልና ሽብርተኝነትን በራሳቸው ለመከላከል የሚያስችል ዓቅም ይፈጥርላቸዋል ተብሎ ይታመናል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም