የአረንጓዴ አሻራ ቀን ሕዝቡ ከመሪው ጎን በመሆን ግቡን ያሳካበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ቀን ሕዝቡ ከመሪው ጎን በመሆን ግቡን ያሳካበት ነው
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 23/2011 በአረንጓዴ አሻራ ቀን ሁለት መቶ ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ትናንት ምሽት ይህንኑ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ህዝብ ቀደም ሲልም ከመሪው ጎን በመቆም በርካታ አገራዊ ጉዳዮችን ያሳካ ሲሆን የአረንጓዴ አሻራ ቀን በአጭር ጊዜና ከታቀደው በላይ እንዲፈጸም ያሳየው ርብርብ ግን "የሚደነቅ" ተብሎለታል። በችግኝ ተከላው በአገር አቀፍ ደረጃ ከ23 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የተሳተፈ ሲሆን ከህጻን እስከ አዋቂ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በንቃት ተሳትፏል። በዚህም በዓለም የክብረ ወሰን መዝገብ በህንድ ተይዞ የነበረውን 66 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር የመትከል ሪከርድ ከቀኑ በ5 ሠዓት ከ30 ማሻሻል መቻሉን ኮሚቴው አስታውቋል። ለዚህ ስኬት ህዝቡ በአጭር ጊዜ የመሪውን ጥሪ ተቀብሎ ቀናኢ ምላሽ መስጠቱ እንደሆነም ነው የኮሚቴው መግለጫ ያብራራው። በአረንጓዴ አሻራ ቀን የሉንም ክልሎች የችግኝ ተከላ መረጃ የሚያሳይ ሶፍትዌር ተዘጋጅቶ በየሰከንዱ ምን ያህል ችግኝ እንደተተከለ በመረጃ ቋቱ እንዲገባ ተደርጓል። ይህም አገሪቷ ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ አፍላቂነት መሸጋገሯን አሳይቷል ተብሏል። የተተከሉ ችግኞች በአግባቡ እንዲጸድቁ ከአተካከል ጀምሮ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ በእያንዳንዱ ችግኝ መትከያ ስፍራ የባለሙያ ድጋፍ ሲሰጥ ውሏል። በቀጣይም የተገኙ መረጃዎች በባለሙያ ትንታኔ እንደሚሰጥባቸው እንዲሁም በቀሪው የክረምት ጊዜ የችግኝ ተከላው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል። ትናንት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች ተተክለዋል።