ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከተነሱ ያሉባቸውን ችግሮች ሁሉ በአሸናፊነት መወጣት እንደሚችሉ የአረንጓዴ አሻራ ቀን አሳይቷል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከተነሱ ያሉባቸውን ችግሮች ሁሉ በአሸናፊነት መወጣት እንደሚችሉ የአረንጓዴ አሻራ ቀን አሳይቷል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 23/2011 ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከተነሱ ያሉባቸውን ችግሮች በአሸናፊነት በመወጣት አገሪቱን ወደብልፅግና ጎዳና ማሸጋገር እንደሚችሉ የ"አረንጓዴ አሻራ ቀን" መርሃ ግብር የህዝብ ተሳትፎ ያረጋገጠው እውነታ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። ትናንት በተካሄደው የችግኝ ተከላ ዘመቻ በኦሮሚያ ክልል ብቻ 212 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ተተክሏል። በትላንትናው እለት አገር አቀፍ አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ ስነ ስርዓት የኦሮሚያ ክልል 2መቶ 12 ሚሊዮን ገደማ ችግኞችን በመትከል ትልሙን ማሳካት ችሏል። የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር የ"አረንጓዴ አሻራ ቀን" የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን ፍፃሜ አስመልክተው ትናንት ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል። በዚሁ መግለጫቸው እንዳሉት በትናንቱ መርሃ ግብር በኦሮሚያ ክልል ብቻ 212 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ተተክሏል። ይህንን አመርቂ ውጤት ለማምጣት የታየው የህዝብ መነሳሳትና የተገኘው ውጤት በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ታላቅ ገድል መሆኑንም አንስተዋል። የክልሉ ህዝብ ለእቅዱ መሳካት ላሳየው ትጋት ምስጋና አቅርበዋል። አያይዘውም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከተነሱ ያሉባቸውን ችግሮች ሁሉ በአሸናፊነት በመወጣት አገሪቱን ወደብልፅግና ጎዳና ማሸጋገር እንደሚችሉ የ"አረንጓዴ አሻራ ቀን" መርሃ ግብር የህዝብ ተሳትፎ ያረጋገጠው እውነታ ነው ሲሉም ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ ገልፀዋል። ይህ ትልቅ ህዝባዊ መነሳሳትና የተመዘገበው ድል ለቀጣዩ የአገሪቱ የልማት ጎዳና መሰረት ሊሆን ይችላልም ብለዋል። ይህንን አመርቂ ድል በሌሎች የስራ ዘርፎችም ለማስቀጠል ቀን ከሌሊት መትጋት ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል። በአጠቃላይ የአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የዚህ ዓይነቱ ትብብር ኃይል ሊሆን ይችላልም ብለዋል። በየደረጃው ያሉት የክልሉ አመራሮችና ህዝቡ በጀመሩት ቁርጠኝነት በመቀጠል የአገርን ኃላፊነት መወጣት አንደሚገባም ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ አንስተዋል። የኦሮሚያ የግብርናና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው በክልሉ ለመትከል የታቀደው የችግኝ ተከላ በታቀደው መሰረት የተከናወነ መሆኑን አንስተው ችግኞቹን የመንከባከብና የማሳደግ ተግባር እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ኢትጵያን አረንግዴ ለማድረግ የተጀመረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ንቅናቄ በሰፊው እየቀጠለ ሲሆን ትናንት ብቻ በመላው ኢትዮጵያ ከ350 ሚሊዮች ችግኞች በላይ ተተክሏል።
ኢትጵያን አረንግዴ ለማድረግ የተጀመረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ንቅናቄ በሰፊው እየቀጠለ ሲሆን ትናንት ብቻ በመላው ኢትዮጵያ ከ350 ሚሊዮች ችግኞች በላይ ተተክሏል።